በመጪዎቹ የትንሳኤና ኤድ በዓላት የኃይል እጥረትና መቆራረጥ እንዳይኖር ከወዲሁ ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በመጪዎቹ የትንሳኤና ኤድ በዓላት የኃይል እጥረትና መቆራረጥ እንዳይኖር ከወዲሁ ዝግጅት ተደርጓል
ሚያዚያ 13/2014 (ኢዜአ) በመጪዎቹ የትንሳኤና ኤድ በዓላት የኃይል እጥረትና መቆራረጥ እንዳይኖር በኃይል ማመንጫና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን ለኢዜአ እንዳሉት፤ ለትንሣኤ በዓል የሚኖረውን የህብረተሰቡን የኤሌክትሪክ ፍላጎት ለማሟላት አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቋል።
ከማከፋፈያ ጣቢያዎች የመነጨውን ኃይል የሚያደርሱ መስመሮችንና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ የሥርጭት ችግር እንዳይኖር ከወዲሁ የዝግጅት ሥራ መከናወኑንም አብራርተዋል፡፡
ያለፉት ዓመታትን የህብረተሰቡን የኃይል ፍላጎት ተሳቢ በማድረግ ከመደበኛው የኃይል አቅርቦት የ2 ነጥብ 7 በመቶ ጭማሪ መደረጉንም ተናግረዋል።
የመረጃ ሥርዓትን የሚያግዝ የኦፕቲካል ግራውንድ ፋይበር መስመርን በማዘጋጀት ሁሉም የማከፋፈያ ጣቢያዎችና ኃይል ማመንጫዎች እንዲሁም መስመሮች በበቂ ሁኔታ ዝግጁ መደረጋቸውን አክለዋል።
ከኃይል አቅርቦቱ በተጨማሪ በኃይል ማመንጫና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ችግር ቢፈጠር ጥገና የሚያደርጉ ባለሙያዎች ዝግጁ ተደርገዋል ብለዋል።
ኀብረተሰቡ በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ በሚፈጸም ሥርቆት የኃይል መስተጓጎል እንዳይከሰት ከሚመለከታቸው የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ሊሰራ እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል።
ህብረተሰቡ ደህንነታቸው የተጠበቀና ኃይል ቆጣቢ የኤሌክትሪክ ቁሳቁሶችን በመጠቀም በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ጥንቃቄ እንዲያደርጉም አሳስበዋል።