የኢትዮጵያና ኤርትራ ሰላም በአፍሪካ ቀንድ የኢኮኖሚ ውህደትን ይፈጥራል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያና ኤርትራ ሰላም በአፍሪካ ቀንድ የኢኮኖሚ ውህደትን ይፈጥራል ተባለ
አዲስ አበባ ጳጉሜ 1/2010 የኢትዮጵያና ኤርትራ ሰላም በአፍሪካ ቀንድ የኢኮኖሚ ውህደትን ይፈጥራል ተባለ። ከረጅም ዓመታት በኋላ በሁለቱ አገራት የተፈጠረውን ሰላም አስመልክቶ “የኢትዮጵያና ኤርትራ ሰላም ለጋራ ብልፅግና” በሚል መርህ ሀሳብ የተዘጋጀውና የአገራቱን ግንኙነትና የተገኘውን ሰላም የተመለከተ በዓል በኩዌት ተከብሯል። የሁለቱ አገራት ወደ ሰላም መመለስ በቀጠናው የኢኮኖሚ ውህደት እንዲፈጠር ጠቃሚ መሆኑንና ከሁለቱ አገራት በዘለለ ለቀጠናው ሰላም ሚና እንዳለው በኩዌት የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተጠባባቂ ጉዳይ ፈጻሚ አቶ አወል አልይ መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ አስታውቋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በሁለቱ አገራት ሰላም እንዲሰፍን ከፍተኛ ሚና እንደነበራቸው በወቅቱ ተገልጿል። በስነ ስርዓቱ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ፓርሜና ማኩዌት ሪያክ በኢትዮጵያና ኤርትራ የተፈጠረው ሰላም ዘላቂነት እንዲኖረው የሁለቱ አገራት ህዝቦች የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል። የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶች እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች መገኘታቸውን ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።