የሕማማት ምሳሌ ለፍጥረት ራስን አሳልፎ በመስጠት ራስን ዝቅ አድርጎ ሌላውን ማገልገል ነው - ቀሲስ ዶክተር ሙሉጌታ ሥዩም - ኢዜአ አማርኛ
የሕማማት ምሳሌ ለፍጥረት ራስን አሳልፎ በመስጠት ራስን ዝቅ አድርጎ ሌላውን ማገልገል ነው - ቀሲስ ዶክተር ሙሉጌታ ሥዩም
ሚያዝያ 13 ቀን 2014 /ኢዜአ/ የሕማማት ምሳሌ ለፍጥረት ራስን አሳልፎ በመስጠት ራስን ዝቅ አድርጎ ሌላውን ማገልገል ነው ሲሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዳሚ ተባባሪ ፕሮፌሰር ቀሲስ ዶክተር ሙሉጌታ ስዩም ተናገሩ፡፡
ቀሲስ ዶክተር ሙሉጌታ ስዩም ሕማማት ለሌላው መጸለይ፣ መራራትና ማዘን እንዲሁም ጠላትን እስከመውደድ የሚያደርስ ስብዕናን የሚያላብስ መሆኑን አመልክተዋል።
በመሆኑም እርስበርስ መለያየትና በጠላትነት መፈራረጅ ክርስትናን ካለመረዳትና ወደ ተግባር መለወጥ ካለመቻል የመነጨ መሆኑንም አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ እየተስተዋሉ ላሉ ማኅበራዊ ስብራቶች ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች በምክንያትነት እንደሚጠቀሱ ገልጸው፤ በተለይ ለራሳችን ባህል፣ እምነትና ማንነት አክብሮት አለመስጠት ዋነኞቹ ውስጣዊ ችግሮች መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
"እኛ ኢትዮጵያዊያን ረዥም ዘመናትን ያስቆጠረ የአብሮነት እሴት አለን" ያሉት ቀሲስ ዶክተር ሙሉጌታ፤ የተለያየ ማንነትና ሃይማኖት ቢኖረንም ደስታና ሀዘንን በጋራ እንካፈላለን ብለዋል።
ለእኛ የሚጠቅመን በመከባበር፣ በመረዳዳትና በወንድማማችነት አንድ ሆነን ቋንቋችንን፣ ባህላችንንና ሃይማኖታችንን አክብረን የውስጥና የውጭ ጠላቶቻችንን መመከት ነው ብለዋል።
እኛ ኢትዮጵያዊያን እርስበርስ በጠላትነት ሳንፈራረጅ ፍቅርና አንድነት እንዲኖረን ልንጸልይ ይገባልም ነው ያሉት፡፡
ሰሞነ ሕማማት የሚያስተምረንን በፍቅር መኖርና መረዳዳት በተግባር መተርጎም እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ይህ ወቅት ክርስቶስ እንዳደረገው ዝቅ ብለን የሌላውን እግር የምናጥብበት፣ የሌላውን ጉድለት የምንሞላበት፣ ትህትናን የምናሳይበት፣ እንዲሁም ፈተናዎች ቢገጥሙንም የምንጸናበት ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።
ቀሲስ ዶክተር ሙሉጌታ አያይዘውም፤ ከክርስቶስ ጽናትን፣ ፍቅርንና ትህትናን ተምረን በእምነትና በሃይማኖት ውስጥ ቀጣይ ሕይወታችንን ብሩህ ልናደርገው ያስፈልጋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የገጠሟት ቀውሶች የነበረንን ባህልና ማንነት አክብረን ማስቀጠል ባለመቻላችን፣ በራስ መተማመን በማጣትና ሌሎችን ለመምሰል በመሞከራችን የተከሰቱ መሆናቸውን አንስተዋል።
ለራስ ባህልና ማንነት ክብር አለመስጠትና ትውልዱንም በዚያ መቅረጽ አለመቻል ጉዳት ማስከተሉን ቀሲስ ዶክተር ሙሉጌታ ገልጸዋል።