ለኢትዮጵያ የማዳበሪያና የእርሻ መሳሪያዎች አቅርቦት ቢልና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን የበኩላቸውን ድጋፍ ያደርጋሉ - ኢዜአ አማርኛ
ለኢትዮጵያ የማዳበሪያና የእርሻ መሳሪያዎች አቅርቦት ቢልና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን የበኩላቸውን ድጋፍ ያደርጋሉ
ሚያዝያ 13/2014 (ኢዜአ) ለኢትዮጵያ የማዳበሪያና የእርሻ መሳሪያዎች በተሻለ ዋጋ እንዲቀርቡ ቢልና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን የበኩላቸውን ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
"በአዲስ አበባ የሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ ኢትዮጵያውያንን ለውትድርና እየመለመለ ነው" በሚል የተሰራጨው መረጃም ስህተት መሆኑን አረጋግጠናል ብሏል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤ በኢኮኖሚ፣ ፖለቲካና ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ላይ በማተኮር ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸውም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፤ ከአፍሪካ ህብረት የፖለቲካ ጉዳዮች የሰላምና ጸጥታ ኮሚሽነር ጋር በሳምንቱ ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።
ኮሚሽነሩም የኢትዮጵያ መንግስት ሰብዓዊ እርዳታ ወደ ትግራይ ክልል እንዲደርስ እያደረገ መሆኑን መረዳታቸውን እንዲሁም የመንግስት አቋም ለሰላም ያለውን ጥረት ያሳየ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከቢልና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን የልማት ፕሬዝዳንት ጋር በተደረገው ውይይትም በትምህርት፣ በጤና እና በግብርና ዘርፎች የተሻለ እንቅስቃሴ መኖሩ ተመልክቷል።
ፋውንዴሽኑ በጤና፣ ትምህርትና የግብርና ዘርፎች የሚያደርገውን ድጋፍ የሚቀጥል መሆኑ በውይይቱ ተነስቷል።
በግጭትና ጦርነት ምክንያት አሁን ላይ ከ24 ሚሊየን በላይ ዜጎች እርዳታ ፈላጊ መሆናቸው የተገለጸላቸው ስለመሆኑም አምባሳደር ዲና ጠቅሰዋል።
የቢልና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን፤ የማዳበሪያና የእርሻ መሳሪያዎችን በተሻለ ዋጋ ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባት "የበኩላችንን ድጋፍ እናደርጋለን" ሲሉ ማረጋገጣቸውንም ገልጸዋል፡፡
የፓርላማና የጤና ባለሙያዎችን የያዘ የእስራኤል የልዑካን ቡድን በጦርነት የወደሙ የጤና ተቋማትን ጎብኝቶ ድጋፍ ማድረጉንም አምባሳደር ዲና አስታውሰዋል።
በቆይታቸው ከፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ ከጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ እና ከአማራ ክልል ፕሬዘዳንት ዶክተር ይልቃል ከፋለ ጋር ውይይት ማድረጋቸውንም እንዲሁ፡፡
በጦርነቱ ምክንያት የወደሙ የጤና ተቋማትን መልሶ ለመገንባት በቀጣይ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ስለ መግባታቸውም ጠቅሰዋል፡፡
"በአዲስ አበባ የሩሲያ ኤምባሲ ወታደራዊ ምልመላ እያደረገ ነው" የሚለውን መረጃ በተመለከተም ፍጹም ሀሰት መሆኑን አምባሳደር ዲና ገልጸዋል።
ከኢምባሲው እንዳረጋገጥነው "ኢትዮጵያውያንን ለወታደርነት እየመለመለ ነው" በማለት የተሰራጨው መረጃ መሰረተ ቢስ ነው፡፡
"የሩሲያ ኤምባሲ አሁን ለማካሄደው ጦርነት በቂ የሰው ሀይል ስላለኝ የማንንም ዜጋ እየመለመልኩ አይደለም" በማለት አረጋግጧል ብለዋል።
ኤምባሲው በቬና ኮንቬንን መሰረት እየሰራ መሆኑን አረጋግጠናል ያሉት አምባሳደር ዲና ምናልባትም በኤምባሲው አካባቢ የታዩ ወገኖቻችን ለሌላ ጉዳይ የሄዱ ሊሆኑ ይችላሉ ሲሉ ተናግረዋል።
በሳኡዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሆኔታ የሚገኙ ዜጎችን ወደ አገራቸው የመመለስ ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቅሰው ባሳለፍ ነው ሳምንት 3 ሺህ ዜጎች መመለሳቸውን አስታውሰዋል።