ቀጥታ፡

የኤጀንሲው መቋቋም የዳያስፖራውን ተሳትፎ የበለጠ ያሳድጋል የሚል እምነት ተጥሎበታል

አዲስ አበባ ጳጉሜ 1/2010 የኢትዮጵያ የዳያስፖራ ኤጀንሲ ሊያቋቁም መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። የኤጀንሲው መቋቋም ዳያስፖራው በአገሪቷ ልማት ላይ የሚያደርገውን ተሳትፎ የበለጠ ለማሳደግ ያስችላል የሚል እምነት ተጥሎበታል። ይህን አስመልክቶም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ መለስ ዓለም ዛሬ  መግለጫ ሰጥተዋል። በዚሁ ጊዜ ኤጀንሲው ሲቋቋም በውጭ አገር ለሚኖሩ ዜጎች በኤምባሲዎችና ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች በኩል ከሚደረግላቸው  ድጋፍ  ባለፈ ወደ አገራቸው ሲመለሱም እስከታችኛው የመንግስት መዋቅር ድረስ አገልግሎት የሚያገኙበትን ሁኔታ የሚያመቻች መሆኑን ቃል አቀባዩ አስታውቀዋል። በውጭ አገሮች የሚኖሩ ዜጎች በአገራቸው ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ የሚኖራቸው ሚና የጎላ መሆኑን የተለያዩ አገሮች ተሞክሮ ያሳያል። ህንድ፣ ጃፓን፣ ሜክሲኮ፣ ቻይና፣ ሞሮኮና ናይጄሪያ የመሳሰሉ አገሮች በውጭ ለሚኖሩ ዜጎቻቸው ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው በመስራታቸው ውጤታማ መሆናቸውንም መረጃዎች ያመለክታሉ። ኤጀንሲው ተጠሪነቱ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሲሆን የራሱ በጀትና የሰው ኃይል ይኖሩታልም ብለዋል። ኤጀንሲው ዋና መቀመጫውን አዲስ አበባ የሚያደርግ ሲሆን እንደየአስፈላጊነቱ በክልሎች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ይኖሩታል። በአሁኑ ጊዜ በአገሪቷ በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ በርካታ የዳያስፖራ አባላት በግልም ሆነ በተናጠል ወደ አገራቸው እየመጡ መሆኑ የኤጀንሲውን መቋቋም የበለጠ ጠቃሚ ያደርገዋል ብለዋል አቶ መለስ። በውጭ የሚኖሩ ዜጎችን መብት ማስከበርና በአገራቸው ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ያላቸውን ተሳትፎ ማሳደግም የኤጀንሲው ሌላ ዓላማ ነው። በኢትዮያ የዳያስፖራ ጉዳይ ትኩረት የተሰጠው ከ1990ዎቹ ዓ.ም ጀምሮ ሲሆን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዳያስፖራ ተሳትፎ ጉዳዮች የሚከታተል ዳይሬክተር ጄኔራል ተቋቁሞ የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል። ለአብነትም በአዲስ አበባ ዙሪያ ብቻ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ሰባት ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ኢንቨስትመንት የዳያስፖራው ነው። ይሁንና ዳያስፖራው በተለያዩ መስኮች ተሰማርተው ውጤታማ መሆናቸው ቢታወቅም የተጠበቀውን ያህል እንዳልሆነ ብዙዎች ያነሳሉ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም