ቀጥታ፡

ኢትዮ- ቴሌኮም የአገር ውስጥ በረራ ትኬት ክፍያን በቴሌ ብር መፈጸም የሚያስችል አሰራር ይፋ አደረገ

ሚያዚያ 12/2014/ኢዜአ/ ኢትዮ- ቴሌኮም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ደንበኞች የአገር ውስጥ በረራ ትኬት ክፍያን በቴሌ ብር እንዲፈጽሙ የሚያስችል አሰራር ይፋ አደረገ፡፡

ኢትዮ-ቴሌኮምና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአገር ውስጥ በረራ ትኬት ክፍያን በቴሌ ብር መፈጸም የሚያስችል ስምምነት አድርገዋል።

ስምምነቱ የአየር መንገዱ ደንበኞች የጉዞ ትኬቶችን ክፍያ ቀላል ፈጣንና ምቹ በሆነ መልኩ እንዲፈጽሙ ያስችላል ነው የተባለው፡፡

አየር መንገዱ በዓመት ከ2 ነጥብ 52 ሚሊዮን በላይ የአገር ወስጥ መንገደኞችን ለማስተናገድ እቅድ ይዞ እየሰራ ሲሆን ፤ የትኬት ክፍያ አገልግሎትን በቴሌ ብር አማካኝነት መጀመሩ ደግሞ ስራውን ይበልጥ ለማሳለጥ እንደሚያግዝ ተገልጿል።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ በዚሁ ወቅት፤ ስምምነቱ ደንበኞች በቀላሉ አገልግሎቱን ለማግኘት እንዲችሉ ያግዛል ብለዋል።

በተጨማሪ እንደ አገር የተጀመረውን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታን እውን ለማድረግ ሚናው የጎላ መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኮሜርሻል ዘርፍ ኃላፊ አቶ ለማ ያዴቻ በበኩላቸው፣ አየር መንገዱ  ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ስምምነት ያደረገው በዋናነት የአገር ውስጥ ደንበኞቹን ተጠቃሚ ለማድረግ ነው፡፡

ይህም ደንበኞች የተቀላጠፈ አገልግሎት ከማግኘት ባሻገር የአገርን ኢኮኖሚ እንደሚደግፍም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

አየር መንገዱ አገልግሎቱን በሙከራ ደረጃ ከጀመረበት የካቲት 7 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ 6 ነጥብ 67 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው የአገር ውስጥ የበረራ ቲኬቶችን በቴሌ ብር አማካኝነት መሸጡን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም