በዞኑ 162 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ካፒታል አስመዝግበው የኢንቨስትመንት ፈቃድ የተሰጣቸው ባለሀብቶች ወደ ስራ ገቡ - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ 162 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ካፒታል አስመዝግበው የኢንቨስትመንት ፈቃድ የተሰጣቸው ባለሀብቶች ወደ ስራ ገቡ
አምቦ ሚያዚያ 12/2014 (ኢዜአ) ባለፉት ዘጠኝ ወራት 162 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ካፒታል አስመዝግበው የኢንቨስትመንት ፈቃድ የተሰጣቸው ባለሃብቶች ወደ ስራ መግባታቸውን በምዕራብ ሸዋ ዞን ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
በዞኑ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የኢንቨስትመንት ፎረም በአምቦ ተካሂዷል፡፡
የምዕራብ ሸዋ ዞን ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ሲርኔሳ በወቅቱ እንደገለጹት፣ በዞኑ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 162 ሚሊየን 500 ሺህ ብር ካፒታል ላስመዘገቡ ለ55 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጥቷል።
ባለሀብቶቹ በዘመናዊ ግብርና፣ በማንፋክቸሪንግና በአገልግሎት የሥራ መስኮች ለመሰማራት የሚያስችላቸውን 4 ሺህ 614 ሄክታር መሬት ተረክበው ወደ ሥራ መግባታቸውን ጠቅሰዋል።
ባለሀብቶቹ በተሰማሩባቸው የልማት መስኮች ለ1 ሺህ 958 ነዋሪዎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን አመልክተዋል ።
እንደ ሃላፊው ገለጻ፣ ጽህፈት ቤቱ በዞኑ ያሉትን የኢንቨስትመንት አማራጮች ለማስተዋወቅ እያደረገ ባለው ጥረት በዘርፉ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት እያደገ መጥቷል።
በዞኑ ባለፉት ዓመታት በኢንቨስትመንት መስክ የተሰማሩ ባለሀብቶች ወደ ምርት ከመሸጋገራቸው ባለፈ የአካባቢውን ኅብረተሰብ በማህበራዊ አገልግሎቶች እየደገፉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በተጨማሪም የሚያመርቷቸውን የግብርና ውጤቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ በማቅረብ የአካባቢውን ሕብረተሰብ ተጠቃሚ እያደረጉ መሆናቸውንም ኃላፊው ገልጸዋል።
በፎረሙ ከተሳተፉት መካከል በጀልዱ ወረዳ በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩት አቶ ጫልቺሳ ኢርኮ እንዳሉት 11 ሄክታር መሬት ላይ የተለያዩ የግብርና ስራዎችን እያከናወኑ ነው።፡
ለ20 ወጣቶችም የስራ እድል መፍጠራቸውን ተናግረዋል።
በዞኑ ባለፉት አመታት ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል አስመዝግበው በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሰማሩ 342 ባለሃብቶች ከ6 ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች የስራ እድል መፍጠራቸውን ከዞኑ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ጽህፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመለክታል።