ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ላይ የሚደርሱ አላስፈላጊ ጫናዎችን ለማስቆም ከኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ጋር አሰራለሁ- ሴናተር ኪም ጃክሰን

ሚያዝያ 12 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ላይ የሚደርሱ አላስፈላጊ ጫናዎችን ለማስቆምና የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላትን በመደገፍ ረገድ ከማህበረሰቡ አባላት ጋር እንደሚሰሩ ሴናተር ኪም ጃክሰን ተናገሩ።

በአሜሪካ አትላንታ የሚገኙ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላት በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙርያ ውይይት አካሂደዋል።

በመድረኩ የተገኙት የጆርጅያ ግዛት ሴናተር ኪም ጃክሰን በሰዎች ዘንድ ሰላምን ለመፍጠር ሁሉም አካል መነሳት አለበት ብለዋል።

"የኢትዮጵያን ማህበረሰብ በመደገፍ ረገድ በሙሉ አቅሜ እሰራለሁ ይህም የሴናተርነት ሃላፊነቴ ነው" በማለት ያስረዱት ሴናተሯ፤ ለአፍሪካ አሜሪካ ባህል መከበር፣ ጥቃት ለሚደርስባቸው ድምጽ ለመሆንና ተጽዕኖችን ለማስቆም ከጎናችሁ በመሆን ድጋፌን አደርጋለሁ ሲሉ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ሴናተሯ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በሰጡት ማብራርያ “ጅምላ ግድያ ተፈጽሟል" በሚል የሚሰነዘሩ የሐሰት ክሶችን እቃወማለው፣ በኢትዮጵያ የተካሄደውን ስድስተኛውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ላለመቀበል ለተደረጉ ጥረቶችም ይቅርታ እጠይቃለሁ፣ የተሳሳተ ድርጊት መሆኑን አመለክታለሁ” ብለዋል።

እዚህ ያላቹ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አንድነታችሁን በማጠናከር እንደ ማህበረሰብ ለመብቶቻችሁ መጠበቅና ለድምጻችሁ መሰማት መስራት አለባችሁም ነው ያሉት።

በቀጣይም ከማህበረሰቡ ጋር በኢትዮጵያ ላይ የሚደርሱ አላስፈላጊ ጫናዎችን ለማስቆም በጋራ መስራት አንችላለን ሲሉ ሴናተር ኪም ጃክሰን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም