ቀጥታ፡

የቱሪዝም ሚኒስቴር የተዳከመውን የቱሪዝም ዘርፍ ለማነቃቃት እየሰራ ነው

ላል ይበላ (ኢዜአ) ሚያዚያ 11/2014 አሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነት እና በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የተቀዛቀዘውን የኢትዮጵያ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ለማነቃቃት እየሰራ መሆኑን የቱሪዝም ሚንስቴር አስታወቀ።

የቱሪዝም እና የሥራና ክህሎት ሚኒስቴሮች የተዳከመውን የቱሪዝም ዘርፍ ለማነቃቃት የሚያስችል የክህሎት ስልጠና በዘርፉ ለተሰማሩ አካላት በላልይበላ ከተማ እየሰጡ ነው።
የቱሪዝም ሚንስትር ዴኤታ አቶ ስለሽ ግርማ በስልጠናው ማስጀመሪያ ላይ እንዳሉት የኮቪድ-19 ወረርሽኝና በአሸባሪው ህወሓት የተለኮሰው ጦርነት የቱሪዝም ዘርፉ በእጅጉ ተጎድቶ ቆይቷል።

በኮሮና ቫይረስና ጦርነቱን ተከትሎም በርካታ ሀገራት ዜጎቻቸው ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመጡ የጉዞ እገዳ መጣላቸውን አስታውሰዋል።

በዚህም የቱሪስት ማዕከላት የነበሩት እንደ ላልይበላ፣ ጎንደር፣ ባህር ዳርና ሌሎች አካባቢዎች የኢኮኖሚ እንቅስቃሴያቸው መጎዳቱን አስረድተዋል።
የተዳከመውን የቱሪዝም ዘርፍ ለማነቃቃት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርቦ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የቱሪስት መስህቦችን ቀድሞ ወደሚሰጡት አገልግሎት ደረጃ እንዲመለሱ በቱሪዝም ዘርፍ ለተሰማሩ አካላት የክህሎት ማሳደጊያ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑንም አስረድተዋል።
ከስልጠናው ባሻገር የጉዞ እገዳ የጣሉ ሀገሮች አምባሳደሮችን በመጋበዝ የቱሪስት መዳረሻ ከተሞችን በማስጎብኘት ውሳኔያቸውን እንዲያስተካክሉ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኤርሚያስ መኮንን በበኩላቸው "የኮሮና ቫይረስና አሸባሪው ህወሓት የከፈተው ጦርነት የክልሉን ቱሪዝም እንቅስቃሴ ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ ቀላል አይደለም" ብለዋል።
በክልሉ የሚገኙ የቱሪስት አገልግሎት ሰጭ ሆቴሎች፣ ተቋማት፣ አስጎኚዎችና በመሰል የሥራ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ወገኖች ከሥራ ውጭ መሆናቸውን አመልክተዋል።
"የተቀዛቀዘውን የቱሪዝም ዘርፍ ለማነቃቃት የክልሉ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው" ያሉት አቶ ኤርሚያስ፣ ስልጠናውም ዘርፉን ለማነቃቃት ሚናው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።
የክህሎት ስልጠናው ለጎብኚዎች የሚሰጠውን አገልግሎት ለማሻሻልና የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን ማልማት በሚያስችል መልኩ የሚሰጥ መሆኑን ገልፀዋል።
በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሰው ሀብት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ በጋሻው ቅጣው በበኩላቸው የቱሪዝም ዘርፉ ከገቢ ማስገኛነት አልፎ ለዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሪያ መሆኑን ተናግረዋል።

የቱሪዝም ዘርፉ በማነቃቃት በዘርፉ ለብዙ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ከቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በጋራ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
በላልይበላ ከተማ እየተሰጠ ባለው የቱሪዝም ክህሎት ስልጠና ላይ በላልይበላ፣ በደባርቅ፣ በጎንደር፣ በባህር ዳር እና በዘጌ ከተሞች በቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ 150 እስጎብኚዎች እየተሳተፉ መሆናቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም