ቀጥታ፡

ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ ተማሪዎችን በውድድር ተቀብሎ ማስተማር ሊጀምር ነው

 ሚያዝያ 11/2014 /ኢዜአ/  ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ከ2015 የትምህርት ዘመን ጀምሮ ተማሪዎችን በውድድር ተቀብሎ ማስተማር ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ፡፡

የቀድሞው ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ከወራት በፊት በአዋጅ ወደ ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ መቀየሩ ይታወሳል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ብርሀነመስቀል ጠና፤ ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የተቋቋመበትን ዓላማ እና የቀጣይ እቅዶች በማስመልከት ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በኢትዮጵያ ከዚህ በፊት የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ባለመኖሩ ለትምህርት ጥራት መጓደል አንድ ምክንያት ሆኖ መቆየቱን ጠቅሰው፤ ችግሩን ለማቃለል ሲባል ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ እውን መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም በተለያዩ ችግሮች እየተፈተነ የሚገኘውን የኢትዮጵያ የትምህርት ዘርፍ ለማከም ከወራት በፊት ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ትልቅ ኃላፊነት ወስዶ ወደ ሥራ ገብቷል ብለዋል።

የመምህራን ዩኒቨርሲቲዎች ዋነኛ ተግባራቸው ለሁሉም የትምህርት ደረጃዎች በየትምህርት አይነቱ መምህራንን ማፍራት መሆኑን ጠቅሰው፤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ግን ከዚህ ከፍ ያለና ሁሉን አቀፍ መሆኑንም አብራርተዋል።

የትምህርት ዩኒቨርሲቲው የመምህራንን ትምህርት ዋነኛ ምሰሶ በማድረግ የትምህርት አመራሮች፣ ተመራማሪዎች፣ አማካሪዎችና ፖሊሲ አውጪዎችን ማፍራት ላይ አተኩሮ ይሰራል ብለዋል።

የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ መንገድና መዳረሻ ምን እንደሆነ የሚያሳይ ፍኖተ ካርታ በዝግጅት ላይ የሚገኝ መሆኑንም ዶክተር ብርሀነመስቀል ገልጸዋል።

በዘንድሮው የትምህርት ዘመን ከነባር የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች በተጨማሪ በትምህርት ሚኒስቴር የሚመደቡለትን ተማሪዎች ተቀብሎ ለማስተማር መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

ከቀጣዩ የትምህርት ዘመን ጀምሮ ግን ዩኒቨርሲቲው ዓላማውን ለማሳካት ያስችለው ዘንድ ተማሪዎችን በፈተና አወዳድሮ በመቀበል ማስተማር ይጀምራል ብለዋል።

ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ተልዕኮውን በብቃት ለመወጣት ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በትብብር የሚሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በተለይም የሰው ኃይል እጥረቱን ለመቅረፍ "የፕሮፌሽናልስ ባንክ" ከፍቶ የትምህርት ዘርፍ ምሁራንን ዝርዝር በማካተት በሚፈለጉበት ሙያ ሁሉ ዩኒቨርሲቲውን እንዲደግፉ የማድረግ እቅድ መኖሩን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም