የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና ኮይካ በጋራ ያሰለጠኗቸው የፈጠራ ባለሙያዎች ተመረቁ - ኢዜአ አማርኛ
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና ኮይካ በጋራ ያሰለጠኗቸው የፈጠራ ባለሙያዎች ተመረቁ
ሚያዝያ 11/2014 /ኢዜአ/ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና የኮርያ ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ /ኮይካ/ በጋራ ያሰለጠኗቸው የፈጠራ ባለሙያዎች ተመረቁ።
የፈጠራ ባለሙያዎቹ በሁለት ዙር የሰለጠኑ ሲሆን ሥራዎቻቸው ችግር ፈቺዎች፣ ለበርካቶች የሥራ እድል መፍጠር የሚያስችሉና ለአገር ኢኮኖሚም ቀጥተኛ አበርክቶ ያላቸው መሆኑ ተገልጿል።
የፈጠራ ባለሙያዎቹ የሥልጠና እድል ያገኙት ከዚህ ቀደም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ባወጣው መሥፈርት መሰረት ተወዳድረው ያለፉ 15 የሥራ ፈጣሪዎች ናቸው።
በተሰጣቸው ሥልጠና መሰረት ዓለም አቀፍ ውድድሮችን በማሸነፍ ከ25 ሺህ እስከ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ሽልማት ያገኙ መሆናቸውም ተጠቁሟል።
በመሆኑም ሚኒስቴሩ ከኮርያ ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ /ኮይካ/ ጋር በመተባበር ለስድስት ወራት በማሰልጠን አስመርቋቸዋል።
በመርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ባይሳ በዳዳ፤ ለወጣቶች አስፈላጊው ድጋፍ ከተደረገላቸው የመፍጠርና የመሥራት አቅም አላቸው ብለዋል።
የዛሬ ተመራቂዎች በግብርና፣ በአገልግሎት፣ በቱሪዝም፣ በማዕድን፣ በቴክኖሎጂ እና ሌሎችም ዘርፎች የፈጠራ ሥራዎችን ያበረከቱ ስለመሆናቸውም ጠቅሰዋል።
በስድስት ወራት የሥልጠና ቆይታቸው ስለ ፈጠራቸው ተጨማሪ ግንዛቤ፣ እውቀት እና ክህሎት ያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይም የፈጠራ ሥራዎቻቸውን ተግባር ላይ በማዋል ራሳቸውን፣ ህዝባቸውንና አገራቸውን የሚጠቅሙ ይሆናል ነው ያሉት።
ከምረቃው አስቀድመው አብዛኞቹ ወደ ሥራ የገቡ መሆናቸውንም ጠቁመው፤ የመነሻ ካፒታል ለሌላቸው የብድር አገልግሎት ይመቻችላቸዋል ተብሏል።
በኮርያ ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ የኢትዮጵያ ተወካይ ሊ ብያግ ሀዎ፤ ኮይካ የቴክኖሎጂ ተኮር ፈጠራ ሥራዎችን የመደገፍና የማበረታታት ፍላጎት እንዳለው ገልጸዋል።
በመሆኑም በኢትዮጵያ የቴክኖሎጂና ሥራ ፈጣሪ ወጣቶችን በዘላቂነት ለመደገፍ የሚሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ከተመራቂዎቹ መካከል የአዋሸ አግሪ ቴክ የፈጠራ ባለቤት አብዲ ጠና፤ በፈጠረው ቴክኖሎጂ በስፋት በመሥራት ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደረግ መሆኑን አረጋግጧል።
የፈጠራ ሥራው አርሶ አደሮች ከመሬት አይነት ጋር የሚስማማ ሰብል ዘርተው እንዲያመርቱ የሚያስችል መሆኑንም ጠቅሷል።
የኢንዱሚን ቴክኖሎጂ ፈጣሪ ሙፈሪሃ አህመድ፤ በተለይም ለትምህርት ዘርፍ የሚጠቅሙ የተለያዩ መተግበሪያዎችን እያበለጸገች መሆኑን ገልጻለች።
ከተመራቂዎቹ ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ደረጃ ለወጡት እንደየደረጃቸው ከምስክር ወረቀት በተጨማሪ ከ3 ሺህ እስከ 300 ዶላር ተሸላሚ ሆነዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከኮይካ ጋር በመተባበር የፈጣራ ባለሙያዎችን ለማበረታታት የ11 ሚሊየን ዶላር የድጋፍ ስምምነት ሥልጠና እየተሰጠ ይገኛል።
ኢትዮጵያና ኮሪያ የቆየ ወዳጅነትና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን፤ ኮይካ ደግሞ በኢትዮጵያ የተለያዩ የልማት ፕሮግራሞችን በማገዝ ይታወቃል።