በአማራና አፋር ክልሎች ከ2 ሚሊዮን በላይ ሠዎች ማህበራዊ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል- የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም - ኢዜአ አማርኛ
በአማራና አፋር ክልሎች ከ2 ሚሊዮን በላይ ሠዎች ማህበራዊ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል- የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም
ሚያዚያ 11 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአማራና አፋር ክልሎች አሸባሪው ህወሃት በፈጸመው ወረራ ከ2 ሚሊዮን 4መቶ ሺህ በላይ ሠዎች ማህበራዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የኢትዮጵያ ህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ገለጸ።
የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በአማራና አፋር ክልሎች ባደረገው የቁጥጥር ዳሰሳ ጥናት ግኝቶች ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ እየሰጠ ነው።
በዚህ ወቅት የተቋሙ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ዘውዱ ወንድም እንደገለፁት የቁጥጥር ጥናቱ በክልሎቹ በጦርነት ምክንያት የተጎዱ ነዋሪዎችን መልሶ ከማቋቋምና ከመንግሥት መቅረብ ያለባቸው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ከማማሏት አኳያ ያሉበትን ደረጃ የዳሰሰ ነው ብለዋል።
አራት ቡድኖችን በማዋቀር በአማራና አፋር ክልሎች በድምሩ 9 ዞኖቹ ላይ የቁጥጥር ጥናቱ ተካሂዷል ነው ያሉት ሃላፊው።
በተቋሙ የሴቶች፣ ህጻናትና አረጋውያን ጉዳዮች ዳይሬክተር ወይዘሮ ቀለመወርቅ ታሪኩ በአማራ ክልል የዳሰሳ ጥናት ግኝቶችን ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት ይህ ዳሰሳ ተቋሙ ለብቻው ያደረገው ነው ብለዋል።
በዚህም ከ1 ሚሊዮን 855 ሺህ በላይ ሠዎች ማህበራዊ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ነው ያሉት።
በጾታዊ ጥቃት ምክንያት የስነ ልቦና ጉዳት የደረሰባቸው በርካታ ሠዎች እንዳሉ ገልፀው 1ሺህ 217 ሰዎች ጥቃት የደረሰባቸው ሲሆኑ እድሜያቸው ከ8 አመት ህፃን እስከ አዛውንት ናቸው ብለዋል፡፡
ከሰብአዊ ጉዳት ባሻገር በሐይማኖት ፣ በግለሰብ፣ በመንግሥትና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት ላይ የንብረት ውድመት፣ ዘረፋና ቃጠሎ ተፈጽሟል ብለዋል።
የዕለት ደራሽ ምግብ ፣ የውስጥ ሰላምን የማረጋገጥ፣ የሥነ ልቦናና ማህበራዊ ድጋፍ እንዲሁም መረጃ የማደራጀት ተግባር ጠንካራ ሥራዎች ነበሩ ሲሉ በመልካምነት አንስተዋል።
በክልሉ ሰሜን ጎንደር ፣ዋግህምራ ሰሜን ሸዋ ዞኖችና ሌሎች አካባቢዎች የሚታየው የጸጥታ ችግር በአፋጣኝ መፈታት አለበትም ተብሏል።
በሌላ በኩል በጦርነቱ ምክንያት ከአፋር ክልል በአጠቃላይ የተፈናቀሉ ከ645 ሺ በላይ ዜጎች ናቸው ያሉት ደግሞ የተቋሙ የምርምር ዳይሬክተር አቶ አዳነ በላይ ናቸው።
6 ሺህ 609 ሠዎች አካላዊ ጥቃት፣ 145ሺ በላይ የስነ ልቦና ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጸው ትምህርት ቤቶች ፣ተቋማት መኖሪያዎች በአስከፊ ሁኔታ ወድመዋል ብለዋል።
እንደ ሆስፒታል ያሉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉና ለሴቶች፣ ህጻናትና አካል ጉዳተኞች የተሰጠው ልዮ ትኩረት በጠንካራ ጎን አንስተዋል።
የሐይማኖት ተቋማት ያበረከቱት ማህበራዊ ድጋፍ ከፍተኛ እንደነበር የተገለፀ ሲሆን ለተፈናቃይ ማህበረሰብ የሚሰጠው ድጋፍ መጠኑ መሻሻል እንዳለበትም ተጠቁሟል።