በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 19ኛ ሳምንት ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ - ኢዜአ አማርኛ
በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 19ኛ ሳምንት ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ
ሚያዚያ 11/2014/ኢዜአ/ በ2014 ዓ.ም የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 19ኛ ሳምንት ሶስተኛ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ይከናወናሉ።
በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ እየተደረገ ባለው 19ኛ ሳምንት ጨዋታዎች፤ ዛሬ ቀን 9:00 ሰዓት አዳማ ከተማ ከሀዲያ ሆሳዕና ይጫወታሉ።
ምሽት 12፡00 ሰዓት ላይ ደግሞ ፋሲል ከነማ ከአዲስ አበባ ከተማ ይጫወታሉ።
ፋሲል ከተማ የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ ካለበት አምስተኛ ደረጃ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ከፍ የሚልበትን እድል ይፈጥራል።
ተጋጣሚው አዲስ አበባ ከተማም በ18 ነጥብ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ያለ ክለብ በመሆኑ ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት ከፍተኛ ፉክክር ያደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።
19ኛ ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በትናንትናው እለት ኢትዮጵያ ቡና ወላይታ ድቻን 1 ለ 0 ሲያሸንፍ ድሬድዋ ከተማ ጅማ አባጅፋርን 2 ለ 1 አሸንፏል።
የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የደረጃ ሰንጠረዥን ቅዱስ ጊዮርጊስ በ41 ነጥብ እየመራ ሲሆን ሲዳማ ቡና በስምንት ነጥብ ዝቅ ብሎ በ33 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ወላይታ ድቻ ከሲዳማ ቡና እኩል 33 ነጥብ ያለው ቢሆንም በግብ ክፍያ ተበልጦ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ሀዋሳ ከተማ በ31 ነጥብ አራተኛ ሲሆን ፋሲል ከነማ በ30 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ሰበታ ከተማ፣ ጅማ አባጅፍርና አዲስ አበባ ከተማ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ናቸው።
ፕሪሚየሪሊጉ በተመረጡ ከተሞች እየተደረገና ከ16 ሳምንት ጀምሮ በአዳማ እየተከናወነ ሲሆን እስከ 21ኛው ሳምንት ያሉ ጨዋታዎች በአዳማ ላይ የሚደረጉ ይሆናል።