በአፍሪካ የሚስተዋለውን የሰላም እጦት በራስ አቅም ለመፍታት የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ ማጎልበት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ የሚስተዋለውን የሰላም እጦት በራስ አቅም ለመፍታት የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ ማጎልበት ይገባል
ሚያዝያ 10 /2014(ኢዜአ) በአፍሪካ የሚስተዋለውን የሰላም እጦትና አለመረጋጋት በራስ አቅም ለመፍታት የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴን ማጎልበት እንደሚገባ የኢትዮጵያና የታንዛኒያ ወታደራዊ መኮንኖች ገለጹ።
የታንዛኒያ ብሔራዊ መከላከያ ኮሌጅ ተማሪዎች በኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ዋና መሥሪያ ቤትና በሰላም ማስከበር ትምህርታዊ ጉብኝት አድርገዋል።
ኮሎኔልና ከዚያ በላይ ወታደራዊ ማዕረግ ያላቸው የታንዛኒያ ብሔራዊ መከላከያ ኮሌጅ ተማሪዎች ከቡሩንዲ፣ ዩጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ናይጄሪያና ከሌሎችም አገሮች የተሰባሰቡ የመከላከያ መኮንኖች ናቸው።
በትምህርታዊ ጉብኝታቸውም የመከላከያ የለውጥ ሥራ፣ የመከላከያ ዋር ኮሌጅና የመከላከያ ዩኒቨርሲቲ በሥልጠና፣ ትምህርትና ትብብር ዙሪያ በሚያከናውኗቸው ተግባራት ላይ ገለጻ ተደርጎላቸዋል።
ከኢፌደሪ መከላከያ የውጭ ግንኙነትና ዓለም አቀፍ ትብብር ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀኔራል ተሾመ ገመቹ፣ የመከላከያ ዋር ኮሌጅ አዛዥ ብርጋዴር ጀነራል ቡልቲ ታደሰ፣ ከመከላከያ ጥናትና ምርምር ማዕከል ሃላፊ ብርጋዴር ጀነራል ይታያል ገላውና ሌሎች መኮንኖች ጋር ተወያይተዋል።
መከላከያ የውጭ ግንኙነትና ዓለም አቀፍ ትብብር ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀኔራል ተሾመ ገመቹ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ በአፍሪካ ምድር ዘላቂ ሰላም ለማስፈን አፍሪካውያን ችግራቸውን በራሳቸው አቅም የሚፈቱበትን ስትራቴጂ መንደፍ አለባቸው።
በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ ከሚከሰቱ ግጭቶች ጀርባ ያለውን ሃቅ መመርመር ይገባል ብለዋል።
በአፍሪካ ምድር ለሚከሰቱ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች መፍትሄ ለመፈለግ በቅድሚያ መንስኤውን በጥልቀት መመርመርና የበለጸጉ አገራት የሚያሳድሩትን ጫና በጋራ መመከት ይገባል ብለዋል።
የታንዛኒያ ብሔራዊ መከላከያ ኮሌጅ ተማሪዎች የጥናት ቡድን ኃላፊ ብርጋዴር ጀነራል ቸለስቲኖ ኤልያስ አፍሪካውያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው መፍታት አለባቸው ብለዋል።
ለዚህም ደግሞ አገራቱ የውስጥ አቅማቸውን ለማዳበር የሚያስችላቸውን የኢኮኖሚ አቅም መፍጠር እንዳለባቸው ነው የገለጹት።
የአውሮፓ አገራት የጋራ በሚያደርጋቸው ቋንቋና ባህል ላይ ቀርቶ ልዩነታቸውን እንኳን በሰከነ መንገድ ነው የሚፈቱት ያሉት የጥናት ቡድኑ ሃላፊ፤ በአፍሪካ ግን በተቃራኒው በማስመሪያ ድንበር ተሰምሯል ብለዋል።
በመሆኑም የአፍሪካ የጸጥታ ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት ጠንካራ አህጉር ለመገንባት ከመከላከያ ሰራዊቱ የሚጀምር የፓን አፍሪካኒዝም ትብብር መኖር አለበት ብለዋል።
የመከላከያ ጥናትና ምርምር ማዕከል ኃላፊ ብርጋዴር ጀነራል ይታያል ገላው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ትናንትም በድል የሚታወቅ ዛሬም በነበረበት ብቃት ላይ ያለ ሰራዊት መሆኑን ገልጸዋል።
አፍሪካውያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው መውጣት እንዲችሉ በሚደረገው ጥረትም ችግር በደረሰ ጊዜ በራሱ መፍታት የሚያስችል አደረጃጀት ላይ እንዳለም ጠቁመዋል።