የሹዋል ኢድ በዓል የቱሪዝም ዘርፉን ለማነቃቃት አስተዋጽኦ አለው - ኢዜአ አማርኛ
የሹዋል ኢድ በዓል የቱሪዝም ዘርፉን ለማነቃቃት አስተዋጽኦ አለው
ሐረር ፣ ሚያዚያ 10/ 2014(ኢዜአ) በሐረሪ ክልል ዘንድሮ ለ1 ሺህ 443ኛ ጊዜ የሚከበረው የሹዋል ኢድ በዓል የተቀዛቀዘውን የቱሪዝም ዘርፍ ለማነቃቃት ራሱን የቻለ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የክልሉ ባህል ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።
ሹዋል ኢድ በየዓመቱ የኢድ አልፊጥር በዓል በተከበረ በሳምንቱ የሚከበረው በዓል ሲሆን፤ በሐረሪ ማህበረሰብ ዘንድ ትልቅ ሥፍራ አለው፡፡
በበዓሉ መላው ዓለም የሚኖሩ ሐረሪዎች፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ቱሪስቶች በብዛት ይካፈሉበታል ፡፡
የቢሮው ኃላፊና የበዓሉ ዓቢይ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተወለዳ አብዶሽ እንደገለጹት በዓሉ ከሀገር ውስጥና ከውጭ በሚመጡ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ይስተናገዱበታል።
በዓሉ ወንድማማችነት፡ ህብረ ብሄራዊ አንድነትና ሀገራዊ ገፅታን ለመገንባት እንደሚረዳም አስረድተዋል።
ሐረር የብሄር ብሄረሰቦች መኖሪያ እንደመሆኗ በዓሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር በማጠናከር ለቱሪዝም ዘርፍ መነቃቃት የጎላ ሚና እንደሚያበረክት አመላክተዋል።
በዓሉን ለማክበር የተለያዩ ኮሚቴዎች መቋቋማቸውን ያመለከቱት አቶ ተወለዳ፣ ከነዚህም የአረንጓዴ ልማትና የፅዳት ሥራዎች እንደሚገኝበት ተናግረዋል።
በሂደት ላይ የሚገኙ ያልተጠናቀቁ ጅምር የልማት ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅም ጥረት እየተደረገ መሆኑን ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡
በየክልሉ የቱሪስት መስህቦችን በእንግዶች ለማስጎብኘት ኮሚቴ መቋቋሙን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም አዲስ የማኑስክሪፕት "ጥንታዊና ረጅም ዕድሜ ያስቆጠሩ ጽሁፎች የሚቀመጡበት/ሙዚዬም እንደሚመረቅ አቶ ተወለዳ ተናግረዋል ፡፡
ከአጎራባች ክልሎች ጋር የቱሪዝም መዳረሻዎችን በጋራ ለማስተዋወቅና ለማበልፀግ እንደሚሰራና የጋራ የባህል ሣምንት እንደሚያዘጋጅ አስታውቀዋል።
እንደ አገር የታየዘውን ከኢድ እስከ ኢድ መርሐ ግብር ለመታደም የሚመጡ እንግዶች በዓሉን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ በሚደረገው እንቅስቃሴ እገዛ እንደሚያደርግም ገልጸዋል፡፡
ሐረር በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ታላቅ ሥፍራ ያላት ታሪካዊ ከተማ መሆኗን የታሪክ መዛግብት ያመለክታሉ።