የቴፒ ከተማ ነዋሪዎች የአስተዳደራዊ አደረጃጀትና መዋቅር ጥያቄያችን ምላሽ ይሰጠው ሲሉ ጠየቁ - ኢዜአ አማርኛ
የቴፒ ከተማ ነዋሪዎች የአስተዳደራዊ አደረጃጀትና መዋቅር ጥያቄያችን ምላሽ ይሰጠው ሲሉ ጠየቁ
ሚዛን ጳጉሜ 1/2010 ለፀጥታ ችግር መንስኤ የሆነው የአስተዳደራዊ አደረጃጀትና መዋቅር መፍትሄ እንዲያገኝ ለመንግስት ያቀረብነው ጥያቄ አፋጣሽ ምላሽ ይሰጠው ሲሉ የቴፒ ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ ። ነዋሪዎቹ ጥያቄያቸውን ያቀረቡት ባካሄዱት ሰላማዊ ሰልፍ ነው ። በሰላማዊ ሰልፉ ለዘመናት የቆየ አስተዳደራዊ በደልና በብሄር ስም የሚፈጸም ተገቢ ያልሆነ ተግባር ይቁም የሚሉና ሌሎች መልእክትቶችም ነዋሪዎቹ ተላልፈዋል ። ከሰልፈኞቹ መካከል ወጣት ደመላሽ ብዙአየሁ እንዳለው ህዝቡ የጠየቀው የፍትህና የአስተዳደራዊ መዋቅር ጥያቄ ፈጣን ምላሽ ሊሰጠው ይገባል፡፡ "ባለፉት ዓመታት በቴፒ ከተማ ተደጋጋሚ ግጭት ተከስቷል" ያለው ወጣት ደመላሽ በክስተቱ የበርካታ ሰው ህይወት ማለፉንና ንብረት መውደሙን አስታውሷል፡፡ ከሰሞኑም በከተማው የተከሰተ ችግር የተፈታ ባለመሆኑ መንግስት የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ አፋጣኝ መፍትሄ እንዲፈልግ ጠይቋል ። አቶ ደበበ በዲ በበኩላቸው "የመዋቅር ጥያቄያችን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ስናቀርብ ቆይተናል" ብለዋል ። መንግስት ለጥያቂያቸው ምላሽ እንዲሰጣቸው ሰላማዊ ሰልፉን ማካሄዳቸውን ተናግረዋል ። በአካባቢው የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ የደቡብ ኢትዮጰያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) ሊቀመንበር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚልን ጨምሮ የክልል ባለስልጣናት የህዝብ መድረኮችን ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ በመድረኮቹ የህዝቡን ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመፍታት መንግስት ኃላፊነት መውሰዱንና የአካባቢው አመራሮችም ከህዝቡ ጋር ተቀራርበው እንዲሰሩ አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል፡፡