በመዲናዋ በጎ ፈቃደኞች ከጸጥታ ኃይሎች ጋር ተቀናጅተው እንዲሰሩ የሚያስችል መመሪያ እየተዘጋጀ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ በጎ ፈቃደኞች ከጸጥታ ኃይሎች ጋር ተቀናጅተው እንዲሰሩ የሚያስችል መመሪያ እየተዘጋጀ ነው
ሚያዝያ 10 /2014(ኢዜአ) በመዲናዋ በጎ ፈቃደኞች ከጸጥታ ኃይሎች ጋር ተቀናጅተው መሥራት የሚያስችል የአሰራር መመሪያ እየተዘጋጀ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ገለጸ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ጸጥታ ቢሮ በቂርቆስ እና አዲስ ከተማ ክፍለ ከተሞች በሰላምና ጸጥታ ማስከበር ዙሪያ የበጎ ፈቃደኞችን ተሳትፎ ማጠናከር የሚያስችል ሥልጠና መስጠት ጀምሯል።
የከተማ አስተዳደሩ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቀንአ ያደታ፤ በመርሃ-ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልእክት የጸጥታ ሥራ በጸጥታ አካላት ብቻ የሚከናወን ባለመሆኑ በመተባበርና በመተጋገዝ መሥራት አለብን ብለዋል።
በመሆኑም በመዲናችን የወንጀል ስጋቶችን በመቀነስ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በተለይም የማህበረሰቡ ተሳትፎ መጠናከር አለበት ያሉት ኃላፊው የመዲናዋ ነዋሪዎች እስካሁን እያደረጉት ላለው የላቀ የሰላምና ጸጥታ ሥራ እገዛና ተሳትፎም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የአዲስ አበባን ሰላምና ጸጥታ አስተማማኝ በማድረግ ሂደት ከማህበረሰቡ የተውጣጡ በጎ ፈቃደኞች ሥልጠና መውሰዳቸው ለሥራው ስኬታማነት ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል ነው ያሉት።
በመሆኑም በጎ ፈቃደኞቹ ከዛሬ ጀምሮ በሁለት ቀናት የሥልጠና ቆይታቸው በሰላም ግንባታ፣ በወንጀል መከላከል፣ በማኅበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎትና ሌሎችም ጉዳዮች ዙሪያ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ይደረጋል ብለዋል።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ ሊዲያ ግርማ በበኩላቸው፤ በጎ ፈቃደኛ የሆኑ የመዲናዋ ነዋሪዎች ከፀጥታ ኃይል ጋር በመቀናጀት የአካባቢያቸውን ሰላም በማስጠበቅ ረገድ እያደረጉ ያለው ተሳትፎ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
የህዝቡን ሰላምና ደህንነት በመጠበቅ ሂደት በጎ ፈቃደኞች ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በመቀናጀት በዘላቂነት እንዲሰሩ የሚያስችል የአሰራር መመሪያ እያዘጋጀ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዘመኑ ደሳለኝ እና የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ እመቤት ተስፋዬ፤ በክፍለ ከተሞቹ የሚፈፀሙ የተለያዩ ወንጀሎችን ለመከላከል ህዝብን ያሳተፈና የተቀናጀ ሥራ ይጠበቅብናል ብለዋል።
በዚህ ዙሪያ ለጸጥታ ሥራው ጉልህ ሚና የሚኖራቸው በጎ ፈቃደኞች መሰልጠናቸው ወሳኝ መሆኑንም ጠቅሰዋል።