በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን የኤሌክትሪክ ቆጣሪ በማስገባትና ምስሶ ተክለው ሃይል ሲያስተላለፉ የነበሩ ተጠርጣሪዎች ተያዙ - ኢዜአ አማርኛ
በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን የኤሌክትሪክ ቆጣሪ በማስገባትና ምስሶ ተክለው ሃይል ሲያስተላለፉ የነበሩ ተጠርጣሪዎች ተያዙ
ሐረር፤ ሚያዚያ 10 ቀን 2014(ኢዜአ) በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን አወዳይ ከተማ በህገ ወጥ መንገድ 400 የኤሌክትሪክ ቆጣሪዎችን በማስገባትና ምስሶ ተክለው ሃይል ሲያስተላለፉ የነበሩ ተጠርጣሪዎች መያዙን ፖሊስ አስታወቀ።
ተጠርጣሪዎቹ በከተማው ከጥቅምት ወር 2013 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያትና ቦታዎች ለግለሶቦች በህገ ወጥ መንገድ የኤሌክትሪክ ቆጣሪዎች በማስገባትና ምስሶ ተክለው ሃይል ሲያስተላለፉ እንደነበር የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ዲቪዥን ሃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ቶሎሳ ጎሹ ተናግረዋል።
ከኢትዮዽያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሐረማያ ቅርንጫፍ ሰራተኛ የሆኑ ጭምር ከተጠርጣሪዎቹ መካከል እንደሚገኙ የገለጹት ሃላፊው የኤሌክትሪክ ቆጣሪዎችን በህገ ወጥ መንገድ አውጥተው ለተለያዩ ነዋሪዎች በማስገባት ሲጠቀሙ እንደነበር አስረድተዋል።
በዚህም ከተጠረጠሩት መካከል ሶስት ግለሰቦች ሲያዙ፤ ተጠርጥረው ለጊዜው ያልተገኙ ሌሎች አምስት ግለሰቦችን ለመቆጣጠር ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑን ነው የተናገሩት።
በተጨማሪም በአወዳይ ገንደ ጨፌ እና ገንደ ሰብሮ ቀበሌዎች ውስጥ በህገ ወጥ መንገድ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የማያውቀው 23 ኤሌክትሪክ ምስሶ ተክለው ሃይል ሲያስተላልፉ የነበሩ ሁለት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቀዋል።
ሌሎች የተጠረጠሩ ሁለት ግለሰቦች ለማግኘት በፖሊስ ክትትል እየተደረገባቸው እንደሚገኝም ዋና ኢንስፔክተር ቶሎሳ ገልጸዋል።
በድርጊቶቹ የተጠረጠሩት ግለሰቦች ጉዳያቸው በዞኑ ከፍተኛው ፍርድ ቤት እየታየ እንደሚገኝ ያስታወቁት ደግሞ የዞኑ አቃቤ ሕግ ጽህፈት ቤት የሙስናና ታክስ ወንጀሎች የስራ ሂደት ባለቤት አቶ ግርማ በለጠ ናቸው።
ስለ ጉዳዩ የኢትዮዽያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሐረማያ ቅርንጫፍን ኢዜአ በተደጋጋሚ በስልክ ለማነጋገር ሞክሮ ማግኘት አልቻለም፤ ሆኖም በቀጣይ ምላሹን እንዳገኘ እንደሚያቀርብ ይገልጻል።