ወደ አገር ውስጥ የሚገባ የአፈር ማዳበሪያ አልፎ አልፎ የኪሎ ጉድለት ይገኝበታል የሚል ቅሬታ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
ወደ አገር ውስጥ የሚገባ የአፈር ማዳበሪያ አልፎ አልፎ የኪሎ ጉድለት ይገኝበታል የሚል ቅሬታ ቀረበ
ሚያዝያ 10/ 2014(ኢዜአ) ወደ አገር ውስጥ የሚገባ የአፈር ማዳበሪያ አልፎ አልፎ የኪሎ ጉድለት እንደሚገኝበት ቅሬታ ቀረበ።
ወደ አገር ውስጥ እየገባ ባለው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ አልፎ አልፎ በሚያጋጥም የኪሎ ጉድለት ማዳበሪያውን በሚያሰራጩ ሕብረት ሥራ ማህበራት እና ከወደብ በሚያመጡ ጭነት ባለንብረቶችን መካከል አለመግባባት እየፈጠረ ይገኛል።
የሕብረት ሥራ ማሕበራት የኪሎ ጉድለት የተገኘበትን የአፈር ማዳበሪያ 'አንረከብም' ሲሉ የጭነት ትራንስፖርት ባለንብረቶች ደግሞ ችግሩ የእነሱ አለመሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን እያንዳንዱ ከረጢት የአፈር ማዳበሪያ ተመዝኖ እንደሚጫን አረጋግጦ፤ በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ውይይት እንደሚደረግም ተናግሯል።
ኢዜአ የአፈር ማዳበሪያው ጭነት ለምን ጎደለ? ሲል የሁሉንም ወገን ያነጋገረ ሲሆን የ'ብራይት' ድንበር ተሻጋሪ ደረቅ ጭነት ባለንብረቶች ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ሲሳይ ንጉስ፤ ማዳበሪያው ከተገዛበት ቦታ በ'ብትን' ጭነት መልክ ተጓጉዞ ጅቡቲ ወደብ ላይ ታሽጎ እንደሚጫን ይገልጻሉ።
ብትኑ ማዳበሪያ በጅቡቲ ወደብ ላይ በማሽን እንደሚታሽግ አስረድተው፤ "እኛ አጓጉዘን ወደ መጋዘን ስናራግፍ አይቀበሉንም፤ መሰረታዊ ችግሩ ግን የማን እንደሆነ አልታወቀም፤ ማዳበሪያው ሳይቀደድ፣ አፉ ሳይፈታና ሳይሸቀሸቅ እንደተሰፋ ከደረሰ ያጓጓዘው አካል ችግር አይሆንም" ብለዋል።
መንግስት ችግሩ ከየት እንደሆነ አጣርቶ ችግሩን የፈጠሩትን ተጠያቂ ለማድረግ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት የተውጣጣ መዋቅር ዘርግቶ በጥናት ማረጋገጥ እንዳለበት ገልጸዋል።
የፌደራል ሕብረት ሥራ ኮሚሽን የሕብረት ሥራ ግብይት ዳይሬክተር ይርጋለም እንየው፤ የአፈር ማዳበሪያው ከወደብ ሲገባ አርሶ አደሩ ዘንድ ሲደርስ በታሸገበት ኪሎ ልክ መሆን እንዳለበት ያነሳሉ።
ያም ሆኖ የኪሎ ጉድለት መታየቱንና ጉድለቱ ሲታሸግም ይሁን መንገድ ላይ ሲጓጓዝ ባልታወቀ ምክንያት ዘንድሮ ብቻ ሳይሆን ከዚህ በፊትም እየተንከባለለ የመጣ ችግር እንደሆነ ገልጸዋል።
ሕብረት ሥራ ማህበራቱ የመጣውን ማዳበሪያ በመመዘን ኪሎም ከጎደለ የጎደለውን መጠን መዝግበው ላጓጓዘው ትራንስፖርት ድርጅት ማረጋገጫ መስጠት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
የአፈር ማዳበሪያው የኪሎ ጉድለት ከገጠመው ማህበራቱ በዚህ ሁኔታ ለአርሶ አደሩ እንደማያቀርቡ ገልጸው፤ የጎደለው ተሞልቶና ታሽጎ 50 ኪሎ ከሆነ 50 ኪሎ ተደርጎ ለአርሶ አደሩ እንደሚቀርብ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ያብባል አዲስ በበኩላቸው ከወደብ ጭነት ሲጫን እያንዳንዱ ከረጢት ተመዝኖ ኪሎው ተረጋግጦ እንደሚጫን አረጋግጠዋል።
ከረጢቱ በሚታሸግበት ወቅት የአንድ ወይም ሁለት ኪሎ ጉድለት አልፎ አልፎ ሊያጋጥም ቢችልም እስከ አምስት ኪሎና ከዛ በላይ የኪሎ ጉድለት ካጋጠመ ግን በማጓጓዝ ላይ የተፈጠረ ችግር ሊሆን ይችላል ባይ ናቸው።
ጉድለት ያለበት የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ መቅረብ የለበትም ያሉት አቶ ያብባል፤ ከጭነት ድርጅቶች ጋር በመነጋገር ችግሩን ለመፍታት እየተሰራ ነው ብለዋል።