የጆሮ ማዳመጫን ያላግባብ መጠቀም ለዘላቂ የመስማት ችግር ሊዳርግ ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የጆሮ ማዳመጫን ያላግባብ መጠቀም ለዘላቂ የመስማት ችግር ሊዳርግ ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል

ሚያዝያ 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) የጆሮ ማዳመጫን (ኢር ፎን) ያላግባብ መጠቀም ለዘላቂ የመስማት ችግር ሊዳርግ ስለሚችል ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ የጤና ባለሙያዎች ያሳስባሉ፡፡
በዚሁ ጉዳይ ኢዜአ ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ የጆሮ፣ የአፍንጫና ጉሮሮ ቀዶ ህክምና ሙያተኞች ጋር ቆይታ አድርጓል።

በኮሌጁ የጆሮ፣ የአፍንጫና ጉሮሮ ቀዶ ህክምና ስፔሻሊስቱ ዶክተር አለነ መሸሻ እንደሚሉት፤ ጆሮ ጥንቃቄ ካልተደረገለት በቀላሉ ሊጎዳ የሚችል የሰውነት ክፍል ነው።
ጆሮ ላይ ጉዳት ከሚያደርሱ ምክንያቶች መካከል በከባድ ጥፊ መመታት፣ ጆሮን ማጽዳት በሚል ምክንያት ሹል ነገሮችን ወደ ጆሮ መክተት ዋነኞቹ እንደሆኑ ጠቅሰዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ከፍተኛ የሆኑ ድምጾች ወይም ከፍተኛ ጩኸት ቀጥታ ወደ ጆሮ ሲገባ የመስማት ችግር ሊከሰት ይችላል ብለዋል።
ለዚህ ደግሞ ድምፅን መጥነው የማያሰሙ የጆሮ ማዳመጫዎችን (ኢር ፎን) መጠቀም ዘላቂ ለሆነ የመስማት ችግር ሊዳርግ እንደሚችልም አንስተዋል።
ሁለት አይነት የጆሮ ማዳመጫዎች መኖራቸውን የጠቀሱት ዶክተር አለነ፤ በሐኪም ከሚታዘዘው የጆሮ ማዳመጫ በስተቀር ሌሎቹ ጥንቃቄ ካልተደረገባቸው ለጉዳት እንደሚዳርጉም ነው ያብራሩት።
ሕብረተሰቡ የጆሮ ማዳመጫን በሚጠቀምበት ጊዜ በተቻለው መጠን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበትም ያሳስባሉ።
በተለይ በጆሮ ቀዳዳ ውስጥ የሚጠለቁ የጆሮ ማዳመጫዎችን ከመጠቀም ጆሮን ሸፍነው ከላይ የሚሆኑትን መጠቀም እንደሚሻል አስገንዝበዋል፡፡
ሌላው በዚሁ ሆስፒታል ከአንገት በላይ ህክምና ክፍል ባልደረባ ዶክተር ፍጹም ኃይለማሪያም በበኩላቸው፤ በጆሮ ማዳመጫዎች ወደ ጆሮአችን የሚሄደው የድምጽ መጠን ካልተመጠነና የርዝማኔው መጠን ካልተወሰነ በጆሮ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ተናግረዋል።

የጆሮ ማዳመጫዎችን በአግባቡ ያለመጠቀም ለጆሮ 'ኢንፌክሽን' አጋላጭ እንደሚያደርግም ነው የጠቀሱት።
እንደ ዓለም ዓቀፉ የጤና ድርጅት ጥናት በአሁኑ ጊዜ ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት ከ100 ሰዎች አምስቱ የተወሰነ የጆሮ የመስማት ችግር አለባቸው ተብሎ ይታመናል።