ቀጥታ፡

‘'ኤችአር 6600’ እና ‘ኤስ 3199’ ረቂቅ ሕጎችን የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ በዋሺንግተን ዲሲ ተካሄደ

ሚያዝያ 10 ቀን 2014 (ኢዜአ)‘ኤችአር 6600’ እና ‘ኤስ 3199’ ረቂቅ ሕጎችን የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ በአሜሪካ ዋሺንግተን ዲሲ ተካሄደ።

ዋይት ሃውስ ፊት ለፊት በተካሄደው ሰልፍ “ማዕቀብ ይገድላል”፣”ጸረ-ኢትዮጵያ፣ኤርትራና አሜሪካ የሆኑትን ረቂቅ ሕጎች እንቃወማለን”፣”‘ኤችአር 6600’ እና ኤስ 3199’ ይሰረዙ” እና ”ፍላጎትን በኃይል ለመጫን የሚደረግ ማንኛውም ድርጊት እንቃወማለን አንቀበልም” የሚሉ መልዕክቶች መተላለፋቸውን ኢዜአ ከሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ ማህበር የዋሺንግተን ግብረ ኃይል ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

ረቂቅ ሕጎቹ ኢትዮጵያን እንዲሁም የኢትዮጵያና አሜሪካን የረጅም ጊዜ ግንኙነት የሚጎዱ በመሆናቸው በፍጥነት መሰረዝ አለባቸው የሚሉ መፈክሮች በሰልፉ ላይ መሰማቱን ተገልጿል።

ሕጎቹ በኢትዮጵያ ሰላምን ለማምጣት እየተደረገ ያለውን ጥረት እውቅና ያልሰጠና የሰላም ሂደቱን አሉታዊ ተጽእኖ የሚያሳድር ነው ብለዋል ሰልፈኞቹ።

‘ኤችአር 6600’ እና ‘ኤስ 3199’ ረቂቅ ሕጎችን በመቃወም በዋይት ሃውስ ፊት ለፊት የሚካሄደው ሰልፍ በቋሚነት በየሳምንቱ እንደሚከናወን የሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ ማህበር የዋሺንግተን ግብረ ኃይል አስታውቋል።

በተያዘዘ ዜና ‘ኤችአር 6600’ እና ‘ኤስ.3199’ ረቂቅ ሕጎችን የሚቃወም ሰልፍ ከነገ በስቲያ በኒው ጀርዚ ግዛት ይካሄዳል።ሰልፉ የ‘ኤስ.3199’ ረቂቅ ሕግ አርቃቂ ሴናተር ሮበርት ሜኔንዴዝ(ኒው ጀርዚ) ቢሮ ፊት ለፊት እንደሚካሄድ ኢዜአ ከኒው ዮርክ ኒው ጀርዚ ተስፋ ለኢትዮጵያ ድርጅት ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

በአሜሪካ የኮንግረስ አባል ቶም ማሊኖውስኪ (ኒውጀርሲ) ዋና አርቃቂነት፣ በያንግ ኪም (ካሊፎርኒያ)፣ ግሪጎሪ ሚክስ (ኒው ዮርክ)፣ ዴቪድ ሲሲሊን (ሮድ አይላንድስ)፣ ብራድ ሼርማን(ካሊፎርኒያ) እና ማይክል ማካውል (ቴክሳስ) ደጋፊነት የተዘጋጀው ‘ኢትዮጵያ ስታብላይዜሽን ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ አክት’ ወይም ኤችአር 6600 ረቂቅ ሕግ የኮንግረሱ የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ተወያይቶበት ለኮንግረሱ መምራቱ የሚታወስ ነው።

የ‘ኤችአር 6600’ ተጓዳኝ ወይም አጋዥ (ኮምፓኒየን ቢል) የሆነው የኢትዮጵያ ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ ፕሮሞሽን አክት ኦፍ 2022’ ወይም ‘ኤስ.3199’ በአሜሪካ ሴናተር ሮበርት ሜኔንዴዝ (ኒው ጀርዚ) ዋና አርቃቂነት፣ በሴናተር ጀምስ ሪስች (ኢዳሆ)፣ በሴናተር ክሪስ ኩንስ (ዴልዌር) እና በሴናተር ቶም ቲሊስ (ኖርዝ ካሮላይና) ደጋፊነት የተዘጋጀ ሲሆን፤ሴኔቱ እ.አ.አ በ2022 ሊመለከታቸው በጊዜ ሰሌዳው ከያዛቸው ረቂቅ ሕጎች አንዱ ሆኖ እንዲካተት መወሰኑ ይታወሳል።

በአሜሪካ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ረቂቅ ሕጎቹ በሕግ አውጪው አካል ድምጽ ተሰጥቶባቸው እንዳይጸድቁ ለማድረግ ሴናተሮችና የኮንግረስ አባላትን በማናገር፣ደብዳቤ በመጻፍ፣ሰላማዊ ሰልፍ በማካሄድ፣ፊርማ በማሰባሰብና በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ዘመቻ በማድረግ ጥረት እያደረጉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም