ዩሪያ የአፈር ማዳበሪያ ከቀጣይ ሣምንት ጀምሮ ወደ አገር ውስጥ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ዩሪያ የአፈር ማዳበሪያ ከቀጣይ ሣምንት ጀምሮ ወደ አገር ውስጥ ይገባል
ሚያዝያ 9 2014(ኢዜአ) ዩሪያ የአፈር ማዳበሪያ በቀጣይ ሣምንት ወደ አገር ውስጥ መግባት እንደሚጀምር የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።
ግብርና ሚኒስቴር በ2014/15 ምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትና ስርጭት ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።
በዚህ ዓመት 12 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ግዥ መፈጸሙን የተጠቆመ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 4 ሚሊዮን ኩንታሉ እስካሁን ወደ አገር ውስጥ መግባቱ ተገልጿል።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሶፊያ ካሳ በዚህ ጊዜ እንደገለጹት፤ መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ የአፈር ማዳበሪያ ግብዓት ግዥ መፈጸሙን ገልጸዋል።
በምርት ዘመኑ 19 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ፍላጎት መኖሩን ጠቁመው በምርት ዘመኑ ከ15 ሚሊየን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለተጠቃሚዎች እንደሚቀርብ ተናግረዋል።
እስካሁን ያልገባውና በተደጋጋሚ ጨረታ የወጣው ከፍተኛ መጠን ያለው የዩሪያ ማዳበሪያም ጅቡቱ ወደብ እየደረሰ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይ ሳምንት ወደ አገር ቤት መግባት ይጀምራል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ያብባል አዲስ በበኩላቸው፤ እስካሁን 4 ሚሊየን ኩንታል ከወደብ ወደ አገር ቤት እየተጓጓዘ መሆኑን ገልጸዋል።
አሁን ላይ በርካታ መጠን ያለው የአፈር ማዳበሪያ ጅቡቲ ወደብ እየደረሰ መሆኑና ማዳበሪያውን ወደ አገር ውስጥ ለማጓጓዝ በቂ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።
በዚህም በየዕለቱ ከ8 ሺህ 500 ሜትሪክ ቶን በላይ የሚሆነውን በጭነት እንዲሁም 1 ሺህ 500 ሜትሪክ ቶኑን ደግሞ በባቡር እንዲጓጓዝ ለማድረግ መታቀዱን ነው የጠቆሙት።
ለዚህም ከ11 የከባድ ተሽከርካሪዎች ድርጅቶችና ከባህርና ሎጀስቲክስ ድርጅት ጋር ውል መፈጸሙን ጠቁመው የማጓጓዝ ሂደቱ ከእነዚህ ተቋማት አቅም በላይ ከሆነ ሌሎች ድንበር ተሻጋሪ የጭነት ተሽከርካሪዎችን ልንጠቀም እንችላለን ብለዋል።
ጭነቱን ለማጓጓዝ ውል የወሰደው የብራይት ድንበር ተሻጋሪ ደረቅ ጭነት ባለንብረቶች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሲሳይ ንጉስ በበኩላቸው በጉዞ ላይ በርካታ ችግሮች ቢኖሩም ማኅበሩ ግብዓቱን በወቅቱ ለማሰራጨት ቅድመ ዝግጅት አድርጓል ብለዋል።
በተለያዩ አካባቢዎች ያጋመጠው የጸጥታ ችግር፣ በአውራጅና ጫኝ በኩል የተፈጠረ የተጋነና ዋጋ፣ ሕገ-ወጥ ኬላዎች፣ መጋዘን ላይ በፍጥነት ያለማራገፍ ከገጠሟቸው ችግሮች መካከል ጠቅሰዋል።
የግብዓት አቅርቦትና ሥርጭቱ እንዳይስተጓጎል መሰል ችግሮችን የሚመለከተው አካል ሊፈታ ይገባል ብለዋል።
በፌዴራል ኅብረት ሥራ ኮሚሽን የኅብረት ሥራ ግብይት ዳይሬክተር ወይዘሮ ይርጋለም እንየው ከወደብ ተጓጉዞ ወደ ማኅበራቱ መጋዘን የሚደርሰውን የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ ለማሰራጨት ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።
በዚህም እስካሁን በየመጋዘኑ ያሉ ግብዓቶች ለተጠቃሚው እንዲሰራጩና መጋዘኖቹ ክፍት ሆነው እንዲጠብቁ፤ ግብዓቱ ከደረሰ በኋላም መጨናነቅ እንዳይኖር በፍጥነት እንደሚከፋፈል ተናግረዋል።