ሰሜን ኮሪያ የኒዩክሌር መርሃ ግብሯን ለማቆም ቁርጠኛ መሆኗን በድጋሜ አረጋገጠች

ጳጉሜ 1/2010 የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ሀገራቸው የኒዩክሌር መርሃ ግብሯን ለማቆም ቁርጠኛ መሆኗን በድጋሜ አረጋገጡ። የኮሪያ ልሳነ ምድር ከኒዩክሌር ጦር መሳሪያ ስጋት ሙሉ በሙሉ ነጻ እንዲሆን ለመስራት ዝግጁ ነን ማለታቸውን ወደ ሰሜን ኮሪያ ያቀናው የደቡብ ኮሪያ ልዑክ ይፋ አድርጓል። በደቡብ ኮሪያ ፕሬዚዳንት የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ቹንግ ኡይ ዮንግ የሚመራ የሀገሪቱ ልዩ ልዑክ ወደ ሰሜን ኮሪያ ዋና ከተማ ፒዮንግያንግ አቅንቶ ከኪም ጆንግ ኡን ጋር ተወያይቷል። አምስት አባላት ያሉት የደቡብ ኮሪያ ልዩ ልዑክ ከፕሬዚዳንት ሙን ጄይ ኢን የተላከ መልዕክት ለሰሜን ኮያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን አድርሷል። የሰሜን ኮሪያው መሪ የኒዩክሌር መርሃ ግብሩን ሙሉ በሙሉ ለማቆም ከአሜሪካም ሆነ ከደቡብ ከሪያ ጋር በቅርበት ለመስራት ፈቃደኛ መሆናቸውን አረጋግጠውልናል ሲሉ የደህንነት አማካሪው ቹንግ  ገልጸዋል። ሁለቱ ኮሪያዎች በፕሬዚዳንት ሙን እና በኪም ለሶስተኛ ጊዜ የሚካሄደውን ውይይት ከፈረንጆቹ መስከረም 18 እስከ 20 ቀን 2018 ድረስ በፒዮንግያንግ ለማዘጋጀት ስምምነት መደረሱን የደህንነት አማካሪው ተናግረዋል። በሁለቱ መሪዎች ውይይት ቅድመ ዝግጅት ላይ በጋራ ለመስራትም መግባባት ላይ መደረሱን ነው የገለጹት። ሙን እና ኪም በቅርቡ ሲገናኙ የኮሪያን ልሳነ ምድር ሙሉ በሙሉ ከኒዩክሌር ስጋት ነጻ ለማድረግ በተግባር እየተከናወኑ ባሉ ስራዎች ላይ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል። በጋራ ለመበልፀግና ዘላቂ ሰላምን በመካከላቸው ለማስፈን እንዲሁም የፓንሙንጆም የሰላም ስምምነት ትግብራ በውይይታቸው እንደሚዳሰስም መረጃዎች ያሳያሉ። ሁለቱ መሪዎች ለሶስተኛ ጊዜ ከሚያደርጉት የፊት ለፊት ውይይት አስቀድሞ በሁለቱም ሀገራት የኤምባሲ ስራዎችን የሚሰሩ ቆንስላ ፅህፈት ቤቶችን ለመክፈት ተስማምተዋል። ምንጭ፦ ዥንዋ  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም