ቀጥታ፡

አፍሪካ ኤሌክትሮኒክ ትሬድ ግሩፕ የምስራቅ አፍሪካ ቅርንጫፍ ቢሮውን በአዲስ አበባ ሊከፍት ነው

ሚያዝያ 8 ቀን 2014 (ኢዜአ)አፍሪካ ኤሌክትሮኒክ ትሬድ ግሩፕ የምስራቅ አፍሪካ ቅርንጫፍ ቢሮውን በአዲስ አበባ ለመክፈት ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታወቀ።

አፍሪካ ኤሌክትሮኒክስ ትሬድ ግሩፕ (ኢ- ትሬድ ግሩፕ) የአፍሪካ ህብረት አባል አገራትን ፍላጎት መሰረት በማድረግ የንግድ ልውውጥን ለማሳለጥና በጋራ ለመስራት የተቋቋመ ኩባንያ ነው።

የኩባንያው ዋና መስሪያ ቤት ሩዋንዳ ኪጋሊ ሆኖ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን እና የንግድ ተቋማትን በማቀፍ በአህጉሩ ኢኮኖሚን ለማሳደግና የስራ እድል ለመፍጠርም ጭምር የሚሰራ መሆኑም ይታወቃል።

በእቅዱ መሰረት ኩባንያው በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ሴቶችና ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ከ600 ሺህ በላይ የጥቃቅንና አነስተኛ የስራ መስኮችን ይፋ የማድረግ ዓላማም አለው።

የኢ- ትሬድ ግሩፕ የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሙሉአለም ስዩም፤ ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ሕዝብ በላይ ላላት አፍሪካ በልማትና የገበያ እድል መልካም አጋጣሚ መሆኑን ይናገራሉ።

አገራቱ የንግድ ትስስራቸውን ከፍ ቢያደርጉ ዓመታዊ የምርት ምጣኔያቸውን ከማሳደግ ባለፈ አቅርቦትና ፍላጎታቸውን ለማጣጣም ትልቅ እድል የሚፈጥርላቸው ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።

በተለይ በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ የሚመረቱ ቁሳቁሶች ሰፊ ገበያ እንዲያገኙና የኢኮኖሚ እድገቱ ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዲኖራቸው ያደርጋሉ ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከ18 የምስራቅ አፍሪካ አገራት ጋር ተወዳድራ የአፍሪካ ኢ- ትሬድ ግሩፕ የምስራቅ አፍሪካ መቀመጫ ሆና መመረጧን ጠቅሰው ይህም ኢትዮጵያን ተጠቃሚ ያደርጋታል ብለዋል።

ኩባንያው በተለይ የጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፉ ውጤታማነት መደላድል ለመፍጠር ከአፍሪካ አገራት መንግስታት ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የአፍሪካ ኤሌክትሮኒክ ትሬድ ግሩፕ እስካሁን ለምዕራብ አፍሪካ በጊኒ፤ ለደቡባዊ አፍሪካ አገራት በስዋቲኒ ቅርንጫፎቹን የከፈተ ሲሆን ለምስራቅ አፍሪካ አገራት ደግሞ በአዲስ አበባ ለመክፈት ተዘጋጅቷል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ

‼️

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

‼️

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

‼️

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

‼️
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም