ቀጥታ፡

ኢዜአ የራሱ የስርጭት አማራጭ ሊኖረው ይገባል- የብዙሃን መገናኛ ዘርፍ አመራሮች

ሀዋሳ፤ ሚያዝያ 8/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት መረጃን ለህዝብ ተደራሽ ለማድረግ እያከናወነ ካለው ተግባር በተጓዳኝ የራሱ የስርጭት አማራጭ እንዲኖረው በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ የብዙሃን መገናኛና ፕሬስ ሴክሬተሪያት ዘርፍ አመራሮች ተናገሩ።

ኢዜአ የተመሰረተበት 80 ዓመት ምክንያት በማድረግ በሀዋሳ ከተማ የተዘጋጀው አውደ ርዕይን የተመለከቱ አመራሮቹ እንዳሉት፤ ኢዜአ የራሱን የስርጭት አማራጭ ማሰብ አለበት።

የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ብሩክ ሀብቴ በሰጡት አስተያየት፤ በሀገራችን የመገናኛ ብዙሀን ባልተስፋፉበትና በቂ የመረጃ ምንጭ ባልነበረበት ወቅት ኢዜአ የተጓዘበትን መንገድ በአውደ ርዕዩ ተመልክቼያለሁ ብለዋል።

በአውደ ርዕዩ ሌሎች የመገናኛ ብዙሀን ልምድ የሚወስዱበት መሆኑንና ኢዜአም በዚህ መልኩ ትኩረት ሰጥቶ ዝግጅቱን ማመቻቸቱ  የሚያስመሰግን እንደሆነ ገልጸዋል።

"መገናኛ ብዙሀን መደጋገፍና መረዳዳት ይኖርባቸዋል ፤ውድድራቸውም ጤናኛ በበጎ እይታ ላይ የተመሰረት መሆን አለበት ፤ ኢዜአ ከአብዛኛው መገናኛ ብዙሀን ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዳለው አውቃለሁ፤ ከኛ ተቋም ጋርም ጥሩ ግንኙነት ነው ያለው" ብለዋል።

የሲዳማ ክልል ፕሬስ ሴክሬተሪያት ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ፊሊጶስ ናሆም በበኩላቸው ፤ ኢዜአ ባለፉት ሰማንያ ዓመታት ቆይታው መረጃ ለህዝብ ከማድረስ ባለፈ ለታሪክ እንዲቆይ በተለያዩ መረጃዎችን ሰንዶ በማኖር ያበረከተው አስተዋጽኦ ጉልህ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢዜአ ለህዝብና ለሀገር ታማኝ በመሆን ሲያገለግል የቆየና ኢትዮጵያ  ዛሬ ለደረሰችበት የዕድገት ደረጃ የድርሻውን የተወጣና እየተወጣ ያለ መሆኑንም ጠቁመዋል።

"ከአውደ ርዕዩ እንደተረዳሁት ሀገራችን አዲስ ቴክኖሎጂ ማስተዋወቅ ስትጀምር ኢዜአ ቀደምት የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ መሆኑን ማወቅ ችያለሁ" ብለዋል።

ኢዜአ አሁን ዓለም በደረሰበት  ደረጃ ራሱን በማዘመንና ከዚህ በላይ ማደግም መሄድም አለበት ብዬ አምናለሁ ያሉት አቶ ፊሊጶስ፤ መረጃን ተደራሽ ለማድረግ ቅርንጫፎቹን በማስፋት እያከናወነ እንዳለው ሁሉ የራሱ የቴሌቪዥን ስርጭት ሊኖረው እንደሚገባ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በዋናው መስሪያ ቤትና በሀዋሳ ቅርንጫፍ ለረጅም ዓመታት ከሪፖርተርነት እስከ አዘጋጅነት ያገለገለውና አሁን የኒያና ሄልዝ ስራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ መሰረት ኪዳኔ  እንዳለው፤ኢዜአ ለሀገር እድገት በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል።

ዛሬ የሚዲያ ተቋማት ከደረሱበት ደረጃ አንጻር ኢዜአ በነበረው መንገድ ከመጓዝ ይልቅ የራሱን የስርጭት አማራጭ በማቋቋም በቴሌቪዥን ጭምር መምጣት እንዳለበት ተናግሯል።

ያኔ እኔ በነበርኩበት ጊዜ ከሰላሳ በላይ ቅርንጫፎች ነበሩ በዛ ወቅት መረጃ ለማድረስ ስንጠቅም የነበረው መሳሪያ ዛሬ ካለው ጋር ሳነጻጽር ይገርመኛል፤ በአውደ ርዕዩ ሲጠቀምባቸው የነበሩ መገልገያ መሳሪያዎችን ማየት መቻሌ ትውስታዬን ቀስቅሶብኛል ነው ያለው።

ለኢዜአ ለውጥና እድገትም የራሱን አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም