ቀጥታ፡

ህገ ወጥ ግንባታ ለማስቆም የተጀመረው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሐረሪ ክልላዊ መንግስት አስታወቀ

ሐረር ፤ ሚያዚያ 8/ 2014(ኢዜአ) በክልሉ ህገ ወጥ ግንባታና የመሬት ወረራን ለማስቆም የተጀመረው ህጋዊ እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሐረሪ ክልላዊ መንግስት አስታወቀ።

የክልሉ መንግስት ዛሬ ለኢዜአ በላከው መግለጫ ላይ እንደገለጸው፤ በክልሉ በመሬት ፍላጎትና አቅርቦት ላይ በሚስተዋል ክፍተት እንዲሁም ለሙስና በተጋለጠ አሰራርና አገልግሎት አሰጣጥ ምክንያት ህገ ወጥ የመሬት ወረራና ግንባታ ተስፋፍቷል።

በተለይ ስግብግብ ባለሀብቶች በመንግስት መዋቅር የተሰገሰጉ ሙሰኞችን በማሳተፍና የመሬት ደላሎችን በማሰማራት ለግል ፍላጎታቸው ሲንቀሳቀሱ ተስተውለዋል።

በዚህም እጅግ ውስን በሆነውና በማይተካው የህዝብና የመንግስት የመሬት ሀብት ያልተገባ ጥቅም እያገኙ መሆኑን መግለጫው አመልክቷል።

ከህገ ወጥ መሬት ወረራና ቤት ግንባታ ጋር በተያያዘ የችግሩን ስፋትና ጥልቀት በመመልከት እልባት ለመስጠት የክልሉ መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑንም አስታውቋል።

የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና አግባብ ያላቸው አካላትን ያካተተ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ተግባር መገባቱን በመግለጫው ተጠቅሷል።

ስራውም በጥናት ላይ የተመሰረተ፣ ሰፊ ዝግጅት የተደረገበት፣ ከፍተኛ ጥንቃቄ የታከለበትና ህብረተሰቡን  ያሳተፈ በመሆኑ ውጤት እየተገኘበት መሆኑን ገልጿል።

አንዳንድ የህብረተሰብ ክፍሎች ህገወጥ ተግባሩ ተገቢ እንዳልነበር በማመን  ያአግባብ የገነቡትና ያጠሩትን በማፍረስ  ለህግ ተገዢነታቸውን በተግባር ማሳየታቸውን ተወስቷል።

ለዚህም የክልሉ መንግስት ልባዊ ምስጋና ማቅረቡን ነው በመግለጫው የተመላከተው።

በህገ ወጥ መንገድ በተገነቡ ከ100 በሚበልጡ ቤቶች ላይ በተያዘው ሳምንት የማፍረስ እርምጃ መወሰዱንም መግለጫው አያይዞ አስታውሷል።

እንደ መግለጫው የክልሉ መንግስት የጀመረውን ህግን የማስከበር ሥራ በቀጣይም አጠናክሮ ይቀጥላል።

በተለይ መሬት አጥረው የያዙና ህግ ወጥ ግንባታ ያከናወኑ ግለሰቦች በፈቃደኝነት እንዲያፈርሱም የክልሉ መንግስት በላከው መግለጫ ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም