ቀጥታ፡

በዲላ ለከተማ ግብርና የሚውል ዘርና የአፈር ማዳበሪያ ተሰራጨ

ዲላ ፣ ሚያዝያ 8/2014 (ኢዜአ) በዲላ ከተማ በ130 ሄክታር መሬት ላይ ለሚካሄደው የከተማ ግብርና የሚውል ዘርና የአፈር ማዳበሪያ መሰራጨቱን የከተማው ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በከተማው “ምግቤን ከጓሮዬ ጤናዬን ከምግቤ” በሚል መሪ ሀሳብ የከተማ ግብርና ማስጀመሪያ ስነ ስርአት ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍሬህይወት አበበ  በስነ ስርአቱ ላይ እንዳሉት  ምግቤን ከደጄ በሚል መርህ የኑሮ ውድነት ጫናን ለማቃለል በሁሉም አካባቢዎች የከተማ ግብርና ማስጀመሪያ  ንቅናቄ እየተካሄደ ነው።

በግቢያችን በምናለማቸው የጓሮ አትክልቶች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የምናደርገውን ትግል ለማሳካትና ጤናን ለመጠበቅ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው መሆኑን ተናግረዋል ።

የምናለማቸውን አትክልትና ፍራፍሬዎች ከቤት ፍጆታ ባለፍ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻል ጠቅሰው ለተፈፃሚነቱ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

የዲላ ከተማ ግብርና ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ ብርሃኑ ሮቤ "በከተማ ግብርና ጥቅል ጎመን፣ ካሮትና ቀይስርን ጨምሮ አምስት አይነት የጓሮ አትክልት እንዲሁም በቆሎና ቦሎቄ ይለማል"  ብለዋል።

በዲላ ከ500 በላይ ነዋሪዎች በከተማ ግብርና መሰማራታቸውን ጠቁመው ለተሳታፊዎች 130 ሄክታር መሬት ማልማት የሚያስችል 1 ሺህ 430 ኪሎ ግራም ዘርና ማዳበሪያ መሰራጨቱን ተናግረዋል።

የግብርና ስራ በጓሮና በመኖሪያ ቤት አካባቢዎች ባለፈ በከተማ በሚገኝ የመንግስትና የግል ተቋማት እንዲሁም በቤተ እምነቶች ቅጥር ግብ ውስጥ እንደሚከናወንም ጠቁመዋል።

የኑሮ ውድነቱን ለማሸነፍ በተለይ ሴቶች በከተማ ግብርና በግንባር ቀደምነት በመሳተፍ የመፍትሄ አካል መሆን እንደሚገባ በከተማ የእናት ልማት ቡድን መሪ ወይዘሮ መዲሃኒት ደሳለኝ ገልጸዋል።

ሴቶች በልማት ቡድን ተደራጅተው ውጤታማ ለመሆን መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበው የግብርና ባለሙያዎች በቅርብ ሆነው ሙያዊ ድጋፍና ምክር  እንዲሰጡ እየተደረገ ነው ብለዋል።

የሃሮሬሳ ቀበሌ የግብርና ልማት ባለሙያ ወይዘርት ራሄል ፀጋዬ እንዳሉት ነዋሪዎች ከመሬት ባለፈ በተለያዩ አማራጮች አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ቦሌቄ እያለሙ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ወይዘሪት ራሄል አክለውም በቀበሌው 10 ሄክታር መሬት አትክልትን ጨምሮ በተለያየ ዘር ለመሸፈን እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም