ሀገራዊ ምክክሩ በልሂቃን ሳይታጠር መላ ህዝቡን ያሳተፈ መሆን አለበት - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክሩ በልሂቃን ሳይታጠር መላ ህዝቡን ያሳተፈ መሆን አለበት
ባህር ዳር፣ ሚያዚያ 8/2014 (ኢዜአ) ሀገራዊ ምክክሩን ከልሂቃን ባለፈ ብዙሀኑን ህዝብ አካቶ ዘላቂ መፍትሄ በሚያመጣ መልኩ ማካሄድ እንደሚገባ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪው ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ገለጹ።
የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ "ብሔራዊ ምክክር፤ መጻኢ እድል ተግዳሮት” በሚል መሪ ሃሳብ ምሁራንን ያሳተፈ የውይይት መድረክ አካሂዷል።
ፕሮፌሰር ባህሩ “የኢትዮጵያ የማንነት ውድቀትና የብሔራዊ ምክክሩ የቀጣይ መንገድ” በሚል ርዕስ ባቀረቡት የመወያያ ጽሁፍ እንዳሉት ብሔራዊ ምክክሩ በልሂቃን ላይ ብቻ የተንጠለጠለ እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።
የብሔራዊ ምክክሩ ልሂቃን በሚባለው ፖለቲከኛና ምሁራን ብቻ የተንጠለጠለ ከሆነ ገና ከጅምሩ ስህተት መሆኑን ተገንዝቦ ማስተካከል የሁሉም ድርሻ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ሀገራችን እስካሁን ላጋጠማት ችግር መንስኤው "እኛ ምሁራንና ፖለቲከኞች ህዝቡን እንዳላዋቂ በማየት እናስተምራለን ብለን በመነሳታችን የመጣ መሆኑንም መገንዘብ ይገባል" ብለዋል።
በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በሚዘጋጁ የውይይት መድረኮች ህዝቡ ችግሩንና እንዲስተካከልለት የሚፈልገውን በተደራጀ አግባብ እየገለጸ ነው።
ህዝቡ በየመድረኩ ችግሩን በመለየትና መፍትሄ እንዴት ማምጣት እንደሚቻል ተንትኖ ሲያቀርብ የዳበረ የውይይት ልምድ እንዳለው ለመገንዘብ እንደማያዳግትም ተናግረዋል።
"እንደ ልሂቃኑ በአየር ላይ የተንጠለጠለ መፍትሄ ሳይሆን መሬት የነካ የመፍትሄ አቅጣጫ በማስቀመጥ እንዲተገበርለት በማስገንዘብ ጭምር መግለጹም እውቀትና ክህሎቱ ህዝብ ጋር መሆኑን የሚያስረዳ ነው" ብለዋል።
በመሆኑም በማንኛውም ሁኔታ ብዙሀኑን ህዝብ አካቶ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ዘላቂ መፍትሄ የሚያመጣ የምክክር መድረክ ማካሄድ እንደሚገባ ፕሮፌሰር ባህሩ ገልጸዋል።
"ሀገራዊ ምክክሩን ስኬታማ ለማድረግ ልምድም ሆነ የመደብ ስሪት በሀገራችን አለ ብሎ ለመናገር አያስደፍርም" ያሉት ደግሞ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ሹመት ሲሻኝ ናቸው።
"እንደ አውሮፓ ያሉ ሀገራት ችግሮችን በውይይት፣ በድርድርና በትብብር መንፈስ እንዲሁም በሰጥቶ መቀበል መርህ በመፍታት ጥቅማቸውን በማጣጣም የአስተሳሰብ አንድነት የሚያመጡበት ልምድ አላቸው፤ በእዚህም ችግሩ ወደ ጽንፍ እንዳይሄድ በቀላሉ ይቆጣጠሩታል" ብለዋል።
በእኛ ሀገር በብሔርና በፖለቲካ ጥቅም የተሳሰረ ግንኙነት መኖር ጥቅሜ ይነካል ብሎ ያሰበ ድርድሩን ወደ ጽንፍ በመውሰድ ችግር እንዳይፈጠር ከወዲሁ የመድረክ መርህ ማስቀመጥ መገደብ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስ ፋኩልቲ ዲን ዶክተር ታዬ ደምሴ በበኩላቸው እንዲህ አይነት የውይይት መድረኮች ገና በአዲስ የተጀመሩ እንጂ የተጠናቀቁ አይደሉም ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችና ምሁራን በቀጣይ በሚካሄዱ ብሔራዊ የምክክር መድረኮች ላይ በንቃት በመሳተፍ ሃሳብ በማዋጣት ለሂደቱ የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
ዩኒቨርሲቲው እንዲህ አይነት መድረክ ሲያዘጋጅ የመጀመሪያው እንዳልሆነና በቀጣይም መሰል መድረኮችን በማዘጋጀት የተቋሙ ምሁራን በሀገራዊ የምክክር መድረኩ ተሳትፏቸው ለማጎልብት እንደሚሰራ አመልክተዋል።
በውይይት መድረኩ የፖለቲካል ሳይንስ፣ የታሪክ፣ የህግና ሌሎች የትምህረት ክፍሎች ምሁራንና ተማሪዎች ተሳትፈዋል።