ቀጥታ፡

በ"ሹዋል ኢድ" በዓል ላይ ለመታደም ወደ ክልሉ የሚመጡ እንግዶችን ተቀብለን ለማስተናገድ ተዘጋጅተናል- ወጣቶች

ሐረር ፤ ሚያዚያ 8 ቀን 2014(ኢዜአ) በ"ሹዋል ኢድ" በዓል ላይ ለመታደም ወደ ሐረሪ ክልል የሚመጡ እንግዶችን ተቀብለው ለማስተናገድ መዘጋጀታቸውን በክልሉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ወጣቶች አስታወቁ፡፡

ወጣቶቹ እንዳሉት፤ ዝግጅታቸው  ሐረር በምትታወቅበት እንግዳ ተቀባይነት ፣ፍቅር እና የወንድማማችነት እሴት ጎልቶ የሚታይበት እንዲሆን ለማስቻል ነው።

የዘንድሮው የ"ሹዋል  ኢድ" የ"ኢድ እስከ ኢድ"  ፕሮግራም አካል በመሆኑ በርካታ እንግዶች የሚጠበቅ መሆኑን ወጣቶቹ ገልጸዋል።

በዚህም የክልሉን ባህልና የመስህብ ሥፍራዎችን   በስፋት ለማስተዋወቅ   ዕድል እንደሚፈጥር ነው ወጣቶቹ ያመለከቱት።

ወጣት ኢሊያስ ተስፋዬ የሀይዳ ወጣቶች ማህበር ፕሬዝዳንት ሲሆን፤  ወጣቱ እንግዶችን ለመቀበል በቂ ዝግጅት ማድረጋቸው ተናግሯል ፡፡

ወጣቱ ለክብረ በዓሉ ወደ ክልሉ የሚመጡ እንግዶችን ማየት ያሉባቸውን ቱሪስት መስህቦች እንዲመለከቱ ብሎም የክልሉን እሴቶች ለማሳየት  ተዘጋጅተው   እየተጠባበቁ መሆኑን  አስታውቋል፡፡

የ"ወሬግ" ወጣቶች ማህበር አባል  አቡበከር ዱሪ በበኩሉ፤ በክብረ በዓሉ ላይ ለሚታደሙ እንግዶች  የጎዳና ላይ የፈረስ ትርኢቶችን ጨምሮ ጥንታዊ  የሃረሪ ማህበረሰብ ባህላዊ  እንቅስቃሴዎችን የሚያሳዩ ዝግጅቶች እንዳሉ ገልጿል፡፡

"ከኢድ እስከ ኢድ " ፕሮግራም ባህላችን የምናሳይበት መልካም እድል ነው ያለችው ደግሞ ወጣት ኢናስ አበዱልሀሚድ ናት።

በዓሉን በድምቀት ለማክበር መዘጋጀታቸውን ገልጻ፤  እንግዶች በሐረሪ ክልል በድምቀት በሚከበረው  የሹዋል ኢድ ክብረ በዓል ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርባለች ፡፡

የወጣት ማህበራቱ ዘንድሮ  ለ1ሺህ 443ኛ ጊዜ በሚከበረው  የ"ሹዋል ኢድ "ክብረ በዓል ላይ መላው የኢትዮጵያ ህዝቦችና ዳያስፖራዎች ብሎም የኢትዮጵያ ወዳጆች እንዲገኙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም