በሶማሌ ክልል ድርቅ ባስከተለው ችግር ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ምግብ ነክ ቁሶች ተከፋፈለ - ኢዜአ አማርኛ
በሶማሌ ክልል ድርቅ ባስከተለው ችግር ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ምግብ ነክ ቁሶች ተከፋፈለ

ጅግጅጋ ፣ሚያዚያ 8/2014(ኢዜአ) በሶማሌ ክልል ድርቅ ባስከተለው ችግር አስቸኳይ ድጋፍ ለሚሹ አንድ ሚሊዮን 300 ሺህ ወገኖች ምግብ ነክ ቁሶች ማከፋፈሉን የክልሉ የአደጋ ስጋት አመራር ቢሮ አስታወቀ።
ለአርባ አምስት ቀናት ፍጆታ እንዲውል የተከፋፈለው ምግብ ነክ ድጋፍ በነፍስ ወከፍ 50 ኪሎ ሩዝ፣ 25 ኪሎ ስኳር፣ ዱቄት 50 ኪሎ፣ ዘይት ባለሶስት ሊትር፣ የጣሳ ወተትና አንድ ኪሎ ቴምር መሆኑን በቢሮው የቅድመ ማስጠንቀቂያ ቡድን አስተባባሪ አቶ በሺር አረብ ለኢዜአ ገልጸዋል።

ድጋፉ የተደረገው የክልሉ መንግሥት በመደበው 500 ሚሊዮን ብር ወጪ ግዢ በመፈፀም መሆኑን አስረድተዋል።
ምግብ ነክ ቁሶች በቆላማ የክልሉ አካባቢዎች በሚገኙ 84 ወረዳዎች ድርቁን ተከትለው ለችግር የተጋለጡ አንድ ሚሊዮን ሦስት መቶ ሺህ ወገኖች መከፋፋሉን አስታውቀዋል።
ድጋፍ በተለይ ህጻናትና ነፍሰ ጡር እናቶች የሚያስፈልጋቸው አልሚ ምግብ ታሳቢ ያደረገ መሆኑ ተመልክቷል።
ድርቁ ያስከተለው ችግር ከባድ በመሆኑ ድጋፉ አሁንም እንደሚያስፈልግ የገለጹት አቶ በሺር ፤ የእንስሳት መኖና የመጠጥ ውሃ እጥረት እንዳለም ጠቁመዋል።
የመጠጥ ውሃ ችግርን ለማቃለል 358 የውሃ ቦቴዎች ተሠማርተዋል ብለዋል።
የክልሉ መንግስት ከራሱ በጀት ከመመደብ ባለፈ የተለያዩ ክልሎች፣ የአዲስ አበባና ድሬዳዋ አስተዳደሮች እንዲሁም ሌሎች ለጋሾች የሚሰጡትን እርዳታ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች በተገቢው ለማድረስ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስተባባሪው ተናግረዋል።
የእንስሳት መኖና የመጠጥ ውሃ ችግር ለማቃለልም ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ ድርቁ ባስከተለው ችግር ከመኖሪያ ቄያቸው የተፈናቁሉትን ጨምሮ ድጋፍ የሚሹ በአጠቃላይ 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሰዎች እንዳሉ ያመለከቱት አስተባባሪው ሁሉንም ለማዳረስ እንደ ወትሮ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን እገዛ ማድረጋቸውን እንዲቀጥሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል በድርቅ ምክንያት ከጀረር ዞን ጉነገዳ ወረዳ ወደ ጅግጅጋ ከተማ ዞሪያ የመጡት አቶ ንምዓን አብድ አብዲላሂ በሰጡት አስተያየት፤ ቀደም ሲል ካገኙት ብርድ ልብስና የቤት ቁሳቁስ ሌላ አሁን ደግሞ የተለያዩ ምግብ ነክ ቁሶች እንደደረሳቸው ተናግረዋል።
ሌላው አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ሚልጋ ከደር ረሺድ ፤ እርዳታው እለት ተእለት የምንመገባቸው ሩዝና ዱቄት ማካተቱ ለፍጆታ በቀላሉ እንድንጠቀም አስችሎናል ብለዋል።