ቀጥታ፡

ማኅበሩ በጦርነቱ በተጎዱ አካባቢዎች 200 የሚሆኑ በጎ ፈቃደኛ የጤና ባለሙያዎችን በማሰማራት የበኩሉን ድጋፍ እያደረገ ነው

ሚያዚያ 7/2014/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ሕክምና ማኅበር በጦርነቱ በተጎዱ አካባቢዎች 200 የሚሆኑ በጎ ፈቃደኛ የጤና ባለሙያዎችን በማሰማራት የበኩሉን ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ አስታወቀ፡፡

ማኅበሩም 58ተኛውን ዓመታዊ  የሕክምና ጉባኤ "ሐኪሞቻችንና የጤና ሥርዓታችን በግጭት ምክንያት  ለሚመጣ የጤና ቀውስ ምላሽ ለመስጠት ምን ያህል ዝግጁ ናቸው"  በሚል መሪ ቃል አከናውኗል።  

የኢትዮጵያ ሕክምና ማኅበር ፕሬዘዳንት ዶክተር ተግባር ይግዛው ጉባኤው በዋናነት በኢትዮጵያ ተከስቶ በነበረው ጦርነት የህክምናው ዘርፍ የሰጠው  ምላሽ ላይ ያተኮረ እንደነበር ገልፀዋል።

በጉባኤው የወደሙ የሕክምና ተቋማትን መልሶ ማቋቋምና በጦርነቱ አካላዊና አእምሯዊ ጉዳት የደረሰባቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች እንዴት መርዳት እንደሚገባ ውይይት ተደርጓል ብለዋል።

ማኅበሩ የሕክምና ባለሙያዎችን ሙያ ለማጎልበት እየሰራ ስላለው ሥራ ውይይት መደረጉንም እንዲሁ።

በዚህም ማኅበሩ ሆስፒታሎችንና የህክምና ተቋማትን በማስተባበር በጦርነቱ ጉዳት ወደ ደረሰባቸው አካባቢዎች 200 የሚሆኑ በጎ ፈቃደኛ የጤና ባለሙያዎችን እንዳሰማራ ገልፀዋል።

በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበርም በጦርነቱ የወደሙ የጤና ተቋማት ድጋፍ እንዲደረግላቸው በማድረግ የበኩሉን ሚና እንደተወጣም ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም በአገር ውስጥ ከሚገኙ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የቂሊንጦና የቆሬ ማገገሚያ ቦታዎች የመድኃኒት፣ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉንና በቀጣይም መሰል ሥራዎች እንደሚሰሩ ገልፀዋል።

በሌላ በኩል ጉባኤው ነባር የሕክምና ባለሙያዎች ከአዲስ ባለሙያዎች ጋር እርስ በእርስ እንዲማማሩ እንደሚያግዝ ዶክተር ተግባር ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሕክምና ማኅበር በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1954 ዓ.ም እንደተመሰረተ ከማኅበሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም