ቀጥታ፡

ሙስሊሙ ማሕበረሰብ የረመዳንን ጾም ምክንያት በማድረግ የተቸገሩ ወገኖችን ሊደግፍ ይገባል

ሚያዚያ 07 ቀን 2014 (ኢዜአ) ሙስሊሙ ማሕበረሰብ የረመዳንን ጾም ምክንያት በማድረግ የተቸገሩ ወገኖችን እንዲደግፍ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጥሪ አቀረበ፡፡

ምክር ቤቱ ካሊድ ፋውንዴሽን ከተሰኘ ግብረሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር ለአቅመ ደካሞች የረመዳን ጾም ማፍጠሪያነት የሚውል ዘይት፣ ቴምር፣ ሩዝና ዱቄት ድጋፍ አድርጓል።

የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጅ ኡመር እንድሪስ በወቅቱ እንደገለጹት፤ የረመዳን የጾም ወር የመተዛዘን፣ የመደጋገፍ እና ከፈጣሪ ምህረት የሚጠየቅበት ወር ነው።

በመሆኑም የሙስሊሙ ማህበረሰብ ረመዳንን ምክንያት በማድረግ ለተቸገሩ ወገኖች ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ድጋፉ ለተቸገሩ ወገኖች በትክክል መድረሱን ማረጋገጥ እንደሚገባም አመልክተዋል።

የካሊድ ፋውንዴሽን አስተባባሪ ካሊድ ናስር በበኩላቸው፤ ፋውዴሽኑ ድጋፉን ያደረገው ከተለያዩ አካላት በማሰባሰብ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በዚህም 200 አቅመ ደካሞችን መደገፍ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በፊትም በተመሳሳይ የአፋር ክልልን ጨምሮ በአዲስ አበባ በቂርቆስ፣ በቦሌ እና በሌሎች ክፍለ ከተሞች አቅመ ደካሞችን የመደገፍ ስራ ሲሰራ መቆየቱንም  አስታውሰው፤ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም