የአሹራ በዓል በትግራይ ነጃሺ ከተማ ይከበራል - ኢዜአ አማርኛ
የአሹራ በዓል በትግራይ ነጃሺ ከተማ ይከበራል
አዲስ አበባ ነሀሴ 30/2010 የአሹራ በዓል ከመስከረም 9 እስክ 11 ቀን 2011 ዓ.ም በትግራይ ክልል ነጃሺ ከተማ ይከበራል። "የአሹራ በዓላችን ለሰላማችን፣ ለአንድነታችንና ለልማታችን" በሚል መሪ ቃል በዓሉ በደማቅ ሁኔታ እንደሚከበር ተገልጿል። የበዓሉን አከባበር አስመልክቶ የኢትዮ ነጃሺ አስጎብኚና የጉዞ ወኪል የስራ ሃላፊዎች ዛሬ በአዲስ አበባ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። በእስላማዊ የቀን አቆጣጠር የዓመቱ የመጀመሪያ ወር ሙሐረም ይባላል። የሙሐረም ወር አሥረኛው ቀን ደግሞ አሹራ ተብሎ ይጠራል፡፡ ሙስሊሞች ይህንን ቀን በየዓመቱ ያከብሩታል። ምክንያቱም አሹራ አላህ ለአደምና ለሐዋ ይቅርታ ያደረገበት፣ ነቢዩ ኑሕ ከጥፋት ውሃ ድነው ከመርከባቸው ወደ ምድር የወረዱበት፣ ነቢዩ ኢብራሂም በሰደድ እሳት ከመቃጠል የዳኑበት፣ ነቢዩ ሙሳ የቀይ ባህርን ሰንጥቀው በመሻገር ወገኖቻቸውን ከፈርዖን አገዛዝ ነፃ ያደረጉበት፣ ነቢዩ ዒሣም የተወለዱበትና ሌሎችም የተለያዩ የአላህ ፀጋዎች የተከሰቱበት ቀን በመሆኑ እንደሆነ ታሪካዊ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በሙስሊሞች ታሪክ ውስጥ በዚሁ ቀን የተፈፀመ ሌላም ድርጊት እንዳለ ይገለጻል ይኸውም የነቢዩ መሀመድ የልጅ ልጅ የሆኑት ሁሴይን በግፍ የተገደሉበት ቀን ነበር። በዚህም የተነሳ ሙስሊሞች ይህንን ቀን በአንድ በኩል የአላህን ጸጋዎች እያሰቡ፤ በሌላ በኩል በሑሴይን ላይ የተፈፀመውን ግድያ በኀዘንና በቁጭት እያስታወሱ በየዓመቱ እንደሚያከብሩት በዘርፉ ጥናት ያደረጉ ምሁራን ይገልጻሉ። የኢትዮ ነጃሺ አስጎብኚና የጉዞ ወኪል ፕሬዚዳንት መምህር ያሲን ራጅኡ እንደገለጹት፤ በዓሉን ማክበር ያስፈለገው በአሹራ በዓል ውስጥ ኢትዮጵያ ያበረከተችውን አስተዋጽኦ ለዓለም ማስተዋወቅ ነው። እስልምና ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ ያደረጉት ንጉስ አል-ነጃሺ በእስላማዊ አቆጣጠር በ615 ዓ.ም በመጀመሪያ ሙሐረም ወር የአሹራ ቀን እስልምናን ለማስፋፋት የተደረገው ጥረት ፈተና በገጠመው ወቅት በነቢዩ መሐመድ የተደረገው ጥሪ ተቀብለው ከመካ የእምነቱን ተከታዮች ወደ ኢትዮጵያ መቀበላቸውን ተናግረዋል። ይህም ኢትዮጵያ በአሹራ በዓል ውስጥ ያላትን አስተዋጽኦ የሚያሳይና ይህንን በማስተዋወቅ ኢትዮጵያ ከታሪኩ በቱሪዝም ዘርፍ ተጠቃሚ እንድትሆን በዓሉን ማክበር እንዳስፈለገ ተናግረዋል። የታሪክ አጥኚና ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል በበኩላቸው በንጉስ አል-ነጃሺ አማካኝነት ኢትዮጵያ እስልምናን ከተቀበለች በኋላ ንጉሱን ለማስታወስ በትግራይ ክልል ውቅሮ ከተማ አካባቢ በስማቸው የአል-ነጃሺ መስጊድ እንደተገባላቸው ያወሳሉ። በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ የእስልምና እምነት ተከታዮች ከአሹራ በዓል ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ያላትን ሚና ማወቅ እንደሚፈልጉና የአል-ነጃሺ መስጊድ መጎብኘት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል። ኢትዮጵያም ይሄን አጋጣሚ በመጠቀም ታሪኩን በማስተዋወቅ በሚሊየኖች ዶላር የሚቆጠር የቱሪዝም ገቢ ማግኘት እንደምትችልም ተናግረዋል። የአል-ነጃሺ መስጊድን በማስተዋወቅና በአጠቃላይ የነጃሺ ከተማን በማልማት የቱሪስት መዳረሻ በማድረግ ኢትዮጵያ ተጠቃሚ የመሆን እድል እንዳላትም ረዳት ፕሮፌሰር አደም አስረድተዋል። በዓሉ ሃይማኖታዊ ሳይሆን ታሪካዊ ይዘት ያለው በመሆኑ የኢትዮጵያ ታሪክና በዓል እንደሆነም አክለዋል። የኢትዮ ነጃሺ አስጎብኚና የጉዞ ወኪል የኩነት አዘጋጅ ስራ አስኪያጅ አቶ ኢብራሂም ከማል መስከረም 9 ቀን 2011 ዓ.ም በአሹራ በዓል ኢትዮጵያ የቱሪዝም ተጠቃሚ በምትሆንበት ሁኔታ ላይ በመቀሌ ከተማ የፓናል ውይይት እንደሚካሄድ ጠቁመዋል። በሶስቱ ቀናት የበዓል አከባበር ኢትዮጵያ በአሹራ በዓል ያላትን ሚናና በኢትዮጵያ የእስልምና እምነት እንዲስፋፋ ያደረገችውን አስተዋጽኦ በስፋት የማስተዋወቅ ስራ ይሰራል ብለዋል። በበዓሉ ላይ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆኑ በተለያዩ ዓለምት የሚገኙ የእምነቱ ተከታዮችና የሌላ እምነት ተከታዮች እንደሚሳተፉም አስረድተዋል። የሳዑዲ አረቢያ፣ ሱዳን፣ ቱርክና ፓኪስታን እንዲሁም አሁን በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል የዲፕሎማሲ ግንኙነት መጀመሩን ተከትሎ በኤርትራ የሚኖሩ የእምነቱ ተከታዮች በበዓሉ ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል። በቀጣይም ታሪካዊቷን የነጃሺ ከተማ የማልማትና የቱሪስት መዳረሻ የማድረግ እቅድ ተይዟል። በኢትዮጵያ የሐረሪ ብሔረሰብ በየዓመቱ የአሹራን በዓል ያከብራል። የሚያከብረውም ሦስት ተግባራትን በማከናወን ነው። አንደኛ በዕለቱ ይጾማል፤ ሁለተኛ በዕለቱ ምሽት በየቤቱ ገንፎ አዘጋጅቶ ቤተሰቡና ጎረቤቶቹ እንዲመገቡ እንዲሁም በየአድባራቱም ገንፎውን ጅቦች እንዲበሉ እንደሚያቀርብላቸው መረጃዎች ያሳያሉ።