በኢትዮጵያ የእንስሳት በሽታ የዘርፉን ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ እየጎዳ መሆኑ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የእንስሳት በሽታ የዘርፉን ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ እየጎዳ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ ነሃሴ 30/2010 በኢትዮጵያ የእንስሳት በሽታ የዘርፉን ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ ክፉኛ እየጎዳው እንደሆነ የኢትዮጵያ እንስሳት ሀኪሞች ማህበር አስታወቀ። የግብርናና እንስሳት ሃብት ልማት ሚኒስቴር የእንስሳት በሽታን ለመከላከል የተለያዩ በሽታ ተከላካይ ክትባቶችን ለማምረት እየተሰራ እንደሆነ ገልጿል። 32ኛ አመታዊ ጉባኤውን ዛሬ በአዲስ አበባ ማካሄድ የጀመረው የኢትዮጵያ እንስሳት ሀኪሞች ማህበር የእንስሳት በሽታ አገሪቱ የሚጠበቀውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንዳታገኝ በማድረጉ የእንስሳት ጤና ላይ መስራት የሚያስፈልግ መሆኑን አስገንዝቧል። የማህበሩ ፕሬዚዳንት ዶክተር በእውቀት ስራው እንደገለፁት፤ ኢትዮጵያ ለእንስሳት ሀብት እርባታ ምቹ የሆነ አየር ንብረት ቢኖራትም በእንስሳት ጤና፣ ዝርያ ማሻሻልና መኖ አቅርቦት ምክንያት በቂ የገበያ ተደራሽነትን እያገኘች አይደለም። እንስሳቱ በቁጥር ደረጃ ብዙ ቢሆኑም በነፍስ ወከፍ ምርታማነት ዝቅተኛ መሆኑን እና ለዚህም ምክንያቱ በተለይ የእንስሳት ጤና ላይ ባለመሰራቱ መሆኑን ገልፀዋል። በአገሪቱ ያለው የእንስሳት ተላላፊ በሽታ የእንስሳቱን የውጭ ገበያ ፍላጎት እየጎዳ እንደሆነ ጠቁመዋል። በአገሪቱ አርብቶ አደር፣ ጥምር ግብርናና የከተማ ግብርና የሚባሉ ሶስት የአረባብ ዘዴዎች መኖራቸውን ጠቁመው ለሶስቱንም ነባራዊ ሁኔታውን መሰረት ያደረገ የእንሰሳት ጤና አጠባበቅ እንደሚያስፈልግ የማህበሩ ፕሬዚዳንት ጠቁመዋል። የግብርናና እንስሳት ሀብት ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ገብረእግዚአበሄር ገብረዮሀንስ በበኩላቸው የእንስሳት ምርታማነትን ለማሳደግ በማለም በሽታ መከላከል ላይ እየተሰራ ስለመሆኑ ተናግረዋል። የበሽታ መከላከሉ ስራ ዋነኛ ተግባር የሆነው ክትባት መስጠት መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታው ክትባት የማምረት አቅም እያደገ መምጣቱን ጠቁመዋል። ለመከላከል የሚሆን 20 የክትባት አይነት ሃገሪቱ እያመረተች መሆኑን እና ለለማንኛውም አየር ንብረት የሚሆን አዲስ ክትባት እያዘጋጀች መሆኑን ጠቁመዋል። ከዚህ ቀደም ወደቆላማ አካባቢዎች ሲላኩ ተጨማሪ ከማቀዝቀዣ ጋር መላክ የነበረባቸውን የክትባት አይነቶችን ያለማቀዝቀዣ ወደአካባቢዎቹ የሚላኩ ክትባቶችን ለማምረት የሚደረገው ሙከራ እየተሳካ እንደሆነም ዶክተር ገብረ እግዚአብሔር ጠቁመዋል።