ቀጥታ፡

ኢዜአ ተደራሽነቱን በማስፋት መረጃን ለህዝብ በፍጥነት ማድረስ እንደሚጠበቅበት ተመለከተ

ሀዋሳ ፤ሚያዝያ 7/2014 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በተወሰኑ አካባቢዎች ሳይወሰን ተደራሽነቱን አስፋፍቶ መረጃን በፍጥነት ለህዝብ ማድረስ እንደሚጠበቅበት ተመለከተ።

ኢዜአ የተመሰረተበትን 80ኛ ዓመት የሚዘክር ዓውደ ርዕይ ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ተከፍቷል።

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ልዩ አማካሪ አቶ ተሰማ ዲማ እንደገለጹት፤ ኢዜአ በሀገሪቱ የሚከናወኑ የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደት መረጃዎችን ለህዝብ በማድረስ በግንባር ቀደምትነት ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

ከተቋሙ ታሪክ መረዳት እንደተቻለው የመገናኛ ብዙሀን እንደ ዛሬው ባልተበረካቱበት ወቅት ቀድሞ የተነሳና ራሱን ከጊዜ ጋር እያዘመነ በመጓዝ ላይ ያለ አንጋፋ  የመረጃ ምንጭ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢዜአ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ መረጃን ለመላው ኢትዮጵያውያን ሲያደርስ እንደቆየም አወስተዋል።

"የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በተወሰኑ አካባቢዎች ብቻ ተወስኖ ሳይቀር ሁሉንም የሀገሪቱ  ክልሎች ተደራሽ በመሆን መረጃን ለህዝብ  በፍጥነት ከማድረስ ባለፈ የክልል መገናኛ ብዙሀን ጋዜጠኞችን በማሰልጠንና በማብቃት ትልቅ ሀላፊነት አለበት" ብለዋል።

የደቡብ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ሀላፊና ወይዘሮ ሰናይት ሰለሞን በበኩላቸው "የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ለሀገራችን ብሎም ለክልላችን እውነተኛ የመረጃ ምንጭ በመሆን እያገለገለ ያለ አንጋፋ ተቋም ነው" ብለዋል።

ኢዜአ ባለፉት ሰማንያ ዓመታት ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዘገባዎችን ለህዝብ ሲያቀርብ መቆየቱንና በሰራቸው ዘገባዎች የዕድሜውን ያህል ስኬታማ  መሆኑን ገልጸዋል።

"በተለይ በደቡብ ክልል ህዝብን ለልማት እንዲተጋ በማድረግ ረገድ የድርሻውን እየተወጣ እንደሚገኝ፤ ከዜና ዘገባ ባለፈ በዘጋቢ ፊልሞቹ ተደራሽነቱን ይበልጥ ያጠናከረና ለተሻለ ለውጥ የሚተጋ ተቋም መሆኑን ለማረጋገጥ እወዳለሁ" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሀገሪቱ አሁን ለደረስችበት እድገት በሙያው ያበረከት አስተዋጽኦ የላቀ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ጸጋዬ ቱኬ ናቸው።

ብዙ የአፍሪካ ሀገራት የራሳቸው መገናኛ ብዙሀን ባልነበራቸው ወቅት ኢዜአ የኢትዮጵያን ህዝብ በማንቃት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።

የኢዜአ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የ80ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ አዳማ፣ በአማራ ክልል ባህርዳር እንዲሁም ዛሬ ደግሞ በሲዳማና ደቡብ ክልሎች ደረጃ  በሀዋሳ  እያከበረ ይገኛል ብለዋል።

ከበዓሉ በላይ ዛሬ እዚህ የተገኘነው ሀገራችን ሰላም ስለሆነችና ሀገር ስላለን ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ ሀገር ሰላም እንድትሆን የሚዲያ ሚና ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደሚዲያ የሀገራችንን ሰላም ለማስጠበቅ በሁሉም ስፍራ ተንቀሳቅሰን ከሰራን ስለተቋሞቻችን መዘከር ብቻ ሳይሆን ህዝባችን የሚፈልገውን ልማት፣ ዲሞክራሲና እድገት ለማረጋገጥ ያስችላል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አስተማማኝ የመረጃ ምንጭ ሆኖ በመቀጠል  ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር፣ ገፅታን ለመገንባት፣ የህዝቦችን እድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥ በሚካሄዱ እንቅሰቃሴዎች ውስጥ የድርሻውን እንደሚወጣ ገልጸዋል።

ኢዜአ የተመሰረተበትን 80ኛ ዓመት መዘከር ብቻ ሳይሆን በ2022 ከአፍሪካ ቀዳሚ የመረጃ ምንጭ ለመሆን የያዝውን ግብ ለማሳካት የሚያከናወናቸው ስራዎች ለማመላከት ጭምር መሆኑን አስታውቀዋል።

በሀዋሳ ዛሬ በተከፈተው የኢዜአ የ80 ዓመት ጉዞ በሚቃኘው ዓውደ ርዕይ ላይ የሲዳማና የደቡብ ክልል አመራሮችና ተጋባዥ እንግዶች የተገኙ ሲሆን ለሶስት ቀናት ለህዝብ  ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም