ቀጥታ፡

ስፖርትን ሰላምና አንድነታችንን ለማጠናከር እንደ ድልድይ ልንጠቀምበት ይገባል

ሚያዝያ 07 ቀን 2014 (ኢዜአ) ስፖርትን ሰላምና አንድነታችንን ለማጠናከር እንደ ድልድይ ልንጠቀምበት ይገባል ሲል የቀድሞው የብሔራዊ ቡድን ቅርጫትና እጅ ኳስ ተጫዋቹ ዘሪሁን ቢያድግልኝ ተናገረ።

ስፖርት ለአእምሮ ጤናና ለአካል ከሚሰጠው ጠቀሜታ በተጨማሪ ማኅበራዊ ትስስርን በማጎልበት ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማፋጠንም ትልቅ ጠቀሜታ አለው።

ስፖርት በሕዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከርም ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለውና ይህንን ትሩፋት ማስፋት እንደሚገባ ነው የመስኩ ተንታኞች የሚገልጹት።

የደቡብ አፍሪካ የመጀመሪያው ጥቁር ፕሬዝዳንትና የነፃነት ታጋዩ ኔልሰን ማንዴላም ስፖርት ዓለምን የመለወጥ ኃይል እንዳለው ነው በአንድ ወቅት የተናገሩት።

ያም ብቻ ሳይሆን ስፖርት ወጣቶችን በቀላሉ በሚረዱት ቋንቋ የሚያግባባ መሆኑን ነው የገለጹት።

የቀድሞው የብሔራዊ ቡድን የቅርጫትና እጅ ኳስ ተጫዋቹ እንዲሁም የወቅቱ ፈረስ ስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዘሪሁን ቢያድግልኝ ስፖርት ያለውን ዘርፈ-ብዙ ጥቅም ይጋራል።

ስፖርት ሃብታም፣ ደሃ፣ ዘር፣ ቀለም፣ ሃይማኖት ሳይለይ ለሰው ልጆች በእኩልነት የሚሰራና ሰዎችን በቀላሉ የሚያሰባስብ ነው ብሏል።

አሁን ላይ እንደ አገር  የገጠመንን የውስጥ ችግር ለመፍታት የስፖርት መድረኮችን በማዘጋጀት ለሰላም ልንጠቀምበት እንደሚገባም ነው የገለጸው።

በጥላቻ ተያይዘን ከምንወድቅ እጅ ለእጅ ተያይዘን ማደግ መልማት አለብን ብሏል።

ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር ስፖርት የሰላም መፍጠሪያ፣ ወዳጅነትና አንድነትን ማጠናከሪያ በማድረግ ትጠቀምበት እንደነበር ገልጿል።

ለአብነትም በ1970ቹ ኢትዮጵያና ሱዳን በመካከላቸው በነበረ አለመግባባት ለመፍታት የሰላም ንግግሮች ሲደረጉ አንዱ የችግሩ መፍቻ መንገድ ሆኖ ሲሰራበት የነበረው ስፖርት ነው ይላል።

በወቅቱ የሱዳን የስፖርት ልዑክ ኢትዮጵያ በመምጣት ለሳምንት ያህል በአምስት የስፖርት አይነት ውድድሮች መደረጉን ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ልዑክ ወደ ሱዳን በማቅናት በተመሳሳይ መልኩ የህዝብ ለህዘብ ወዳጅነት ለማጠናከር እንደተሰራበትና ጥሩ የሚባል ውጤትም ማስገኘቱን  ተናግረዋል።

በተመሳሳይ በ1960ዎቹ ውስጥ በየዓመቱ ከኬንያ ጋር የአገራቱን ወዳጅነት ለማጠናከር የሚያስችል የቅርጫትና የመረብ ኳስ ጨዋታ ይደረግ እንደነበረም ነው የገለጸው።

እንደ ዘሪሁን ገለጻ፤ አሁን ላይ ኢትዮጵያ የገጠማትን ውስጣዊ ችግር ለመፍታትና ሰላም ለማስፈን ስፖርትን እንደ አማራጭ ልትጠቀምበት ይገባል ነው ያለው።

ለዚህም የስፖርት አመራሩን ጨምሮ ፌዴሬሽኖች፣ ክለቦችና ባለሙያዎች የበኩላቸውን ማድረግ እንደሚገባቸው በመጠቆም።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም