ቀጥታ፡

የጤፍን ምርት የጥራት ደረጃና ብራንድ ወጥቶለት ለውጭ ገበያ ማቅረብ ከተቻለ አምራቹን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው

ሚያዝያ 07 ቀን 2014 (ኢዜአ) የጤፍ ምርት የራሱ የጥራት ደረጃና ብራንድ ወጥቶለት ለውጭ ገበያ ከቀረበ በተለይም አምራቹን አርሶ አደር ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ገለጸ።

የግብርና ሚኒስቴር በበኩሉ የጤፍን ምርት ጨምሮ ማንኛውም ሰብል ወደ ውጭ እንዳይላክ የሚከለክል ሕግ የለም ይላል።

ጤፍ ከቅድመ ልደተ ክርስቶስ ጀምሮ ኢትዮጵያዊያን ያላመዱት ውልደትና ዕድገቱ ኢትዮጵያ በቀል የሆነ የምግብ ሰብል ነው።

በረድኤትና በረከቱ ብሎም በያዛቸው ንጥረ ነገሮች ተመራጭ የሆነው ጤፍ እንደዋዛ ከኢትዮጵያ አፈትልኮ ወጥቶ በርካታ አገራት እያራቡትና እሴት እየጨመረበት ዝናው በዓለም ገበያ ናኝቷል።

በዓለም ላይ ተፈላጊነቱ እየናረ የመጣው ጤፍ የኢትዮጵያን ጤፍ አምራች ገበሬ ተጠቃሚ አላደረገም በሚል ምርቱ ወደ ውጭ ገበያ እንዲቀርብ ሀሳብ የሚያነሱ ብዙ ናችው።

ከጤፍ ዘመናትን የማለፉ ልዩ ባህሪው አንጻርና የኢትዮጵያ ህዝብ ከሌሎች ሰብሎች በተለየ ክፉ ቀንን የሚያልፍበት አለኝታው ጤፍ በመሆኑ ወደ ውጭ መላክ የለበትም የሚሉም አሉ።

እነዚህ ወገኖች በምግብነቱ ተወዳጅና ሁለገብ የሆነው ጤፍ ዋጋ ማናር ሸማቹን የሚያማርር በመሆኑ በውጭ አገር ሳይሆን በአገር ውስጥ ተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርብ ይሻሉ።

ይህን ሃሳብ ግን ከጤፍ የምርት ሂደቱ ውስብስብና አድካሚነት ምርታማ ባለመሆኑ ከሌሎች ሰብል አምራች ገበሬዎች አንጻር ጤፍ አምራቹ ተገቢውን ዋጋ አላገኘም፤ በውጭ ገበያ ልኮ ተጠቃሚ ይሁን በሚሉ ወገኖች ይተቻል።

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ይፍሩ ታፈሰ፤ የጤፍ ምንጭ ኢትዮጵያ ብትሆንም በአሜሪካና ሌሎችም አገሮች በስፋት እየተመረተ ነው ይላሉ።

አገራቱ ጤፍን በምርምርና በቴክሎጂ እያገዙ ወደ ሜካናይዜሽን በመለወጥ ምርታማነቱን እያሳደጉ ሲሆን በኢትዮጵያ ግን በምርምር ረገድ በሚፈለገው ደረጃ አልታገዘም ይላሉ።

በመሆኑም የጤፍ ምርት የራሱ ሕግና ስርዓት ተበጅቶለት በተሻለ ዋጋ ለውጭ ገበያ ቢቀርብ በተለይም አምራቹን ተጠቃሚ የሚያደርግ እንጂ ጉዳት አይኖረውም ባይ ናቸው።

በኢንስቲትዩቱ የአማራ ክልል የግብርና ኮማይርሻላይዜሽና ፕሮጀክቶች ዳይሬክተር ክንዴም አይሸሽም፤ የጤፍ ምርታማነት ከበቆሎና ስንዴ አንጻር ሲታይ አነስተኛ መሆኑን ይናገራሉ።

የጤፍ የምርት ሂደት ከዘር እስከ አጨዳ እና መውቃት ያለው ሰንሰለት በቴክኖሎጂ ባለመደገፉ አድካሚ ሲሆን የግብርና ግብአት የዋጋ ንረትም ለገበያ አዋጭነቱ አነስተኛ ያደርገዋል።

በመሆኑም አምራቹን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሌሎች ሰብሎች ሁሉ የጤፍ ምርት የራሱ የጥራት ደረጃ ወጥቶለት ለውጭ ገበያ መቅረብ ይኖርበታል ብለዋል።

በኢንስቲትዩቱ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ኅላፊ አበበ ድሪባ፤ የጤፍ አምራች አርሶ አደሮች አሁን ባለው ገበያ ተጠቃሚ አለመሆናቸውን ይናገራሉ።

በተሟላ ቴክኖሎጂ ፓኬጅ ምርት በሄክታር በአማካይ 8 ኩንታል  ወደ 20 ኩንታል ማሳደግ ቢቻልም ከማምረቻ ዋጋው አንጻር ተገቢውን ዋጋ እንዳላገኘ ገልጸዋል።

ከህዝብ ቁጥር ጋር ተያይዞ የጤፍ ምርት ፈላጊዎችና ተጠቃሚዎች ቁጥር በመጨመሩ ምርቱን የማሳደግ ስራም ያስፈልጋል ነው ያሉት።

የጤፍ ተፈላጊነት በውጭ አገራትም እየጨመረ በመምጣቱ ኤክስፖርት በማድረግ ለአገርም ለአምራቹም የተሻለ ጥቅም እንዲያስገኝ መስራት ይገባል ብለዋል።

በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ኤክስቴንሽን ዳይሬክተር ጀኔራል ግርማሜ ጋሩማ፤ ከኢትዮጵያ ኤክስፖርት እንዳይሆን በሕግ የተከለከለ ምንም ሰብል እንደሌለ ይገልጻሉ።

በመሆኑም ፈቃድ የወሰዱ አርሶ አደሮችና ባለሀብቶች ምርቱን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የጤፍ ምርት የአመራረት ሂደትና የግብርና ግብአት ዋጋ መናር አምራቹን ተጠቃሚ አላደረገውም የሚለው ሃሳብም ትክክል አይደለም ይላሉ አቶ ግርማሜ።

“አንድ ኩንታል ጤፍ ለማምረት 2 ሺህ ብር በቂ ነው” የሚሉት ዳይሬክተር ጄኔራሉ የንግድ ስርዓቱ የሚፈጥርው ችግር ግን አምራቹም ተጠቃሚ ያላደረገ የዋጋ ንረት አስከትሏል ብለዋል።

የጤፍ ሰብል አሰባሰብና አመራረት ለቴክኖሎጂ የሚመች ባይሆንም ከሌላ ሰብል አመራረት የተለየ አድካሚ አይደለም ይላሉ።

መጠኑ ከፍተኛ ባይባልም ጤፍ ወደ ውጭ እንደሚላክ ገልጸው አገራዊ ችግር በገጠመ ጊዜ ግን እንኳን ጤፍ ሌላ የገበያ ሰብልም ወደ ውጭ እንዳይወጣ ይታገዳል ብለዋል።

በመሆኑም የጤፍን ምርት ቀጥታ ለውጭ ገበያ ከማቅረብ ባለፈ እሴት ጨምሮ በመላክ የተሻለ ተጠቃሚ መሆን ይቻላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም