ቦርዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያቀርቡትን አቤቱታ በመመርመር አጣሪ ቡድን አቋቅሞ ውሳኔ እንዲያገኙ የሄደበት መንገድ ተስፋ ሰጪ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ቦርዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያቀርቡትን አቤቱታ በመመርመር አጣሪ ቡድን አቋቅሞ ውሳኔ እንዲያገኙ የሄደበት መንገድ ተስፋ ሰጪ ነው
አዲስ አበባ ሚይዝያ 6/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያቀርቡትን አቤቱታ በመመርመር አጣሪ ቡድን አቋቁሞ ውሳኔ እንዲያገኙ የሄደበት መንገድ ተስፋ ሰጪ መሆኑን የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አካሂዷል፡፡
በውይይቱም ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባለፉት ጊዜያት የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያቀርቧቸውን አቤቱታዎች ሰባት አጣሪ ቡድን በማቋቋም የማጣራት ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ገልጿል፡፡
በውይይቱ የፓርቲዎቹን አቤቱታ እንደ መነሻ ይዞ አቤቱታው የቀረበባቸው አካባቢዎች ድረስ በመንቀሳቀስና በማጣራት ህጋዊ መፍትሔ እንዲሰጠው ማድረጉም ተገልጿል፡፡
የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ፤ ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሲያሥተዳድር የመሪዎች እና የአባሎቻቸውን ደህንነት የማረጋገጥ ሃላፊነቱን በማወጣት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
በዚህም ባለፉው ታውጆ ነበረውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሰረት በማድረግ ፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ የሚደርሰውን ችግር ለመመርመር ሰባት አጣሪ ቡድኖችን አዋቅሮ ሲሰራ እንደቆየም ገልጸዋል፡፡
ከአጣሪ ቡድኑ መካከልም በኦሮሚያ ክልል የ'ኦፌኮ'ና 'ኦነግ' ፓርቲዎች ያቀረቡትን አቤቱታ ለመመርመር የተቋቋመው አጣሪ ቡድን በክልሉ 29 ወደ ሆኑ ማረሚያ ቤቶች በመሄድ የማጣራት እና መመርመር ስራዎችን እንደሰራም ጠቁመዋል፡፡
በአጣሪ ቡድኑ አማካኝነትም ቦርዱ የተሰጠውን ሃላፊነት በሚገባ ሲወጣ መቆቱንም ተናግረዋል፡፡
በወይይቱ ወቅት አስትያየት የሰጡ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና ተወካዩች ምርጫ ቦርድ ህግን ለማስከበር እና በአገሪቷ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲጎለብት እያደረገ ያለው ተግባር ተስፋ ሰጪ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ቦርዱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ታሪክ በተሻለ መልኩ እየቀየረ መሆኑንም መታዘባቸውን ገልጸዋል፡፡
አስትያየት ሰጪዎቹ ቦርዱ የፓርቲዎችን ቅሬታ በመውሰድ ለሰራው ስራ ምስጋናም ይገባል ብለዋል፡፡
በአገሪቷ በጅምር ላይ ላለው የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መጎልበት ከፖለቲካ ፓርቲዎች የሚቀርቡ ቅሬታዎችን ታች ወርዶ እያየ ያለበት ሁኔታም ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በሌላ በኩል ''በአጣሪ ቡድኑ ታይተው መፍትሄ ያላገኙ ጉዳዮችን ቦርዱ የሚመለከተው አካል ጋር በመሄድ መፍትሄ ቢያስጥ'' የሚል ሀሳብም አንስተዋል ተሳታፊዎቹ፡፡
በተለይም ያለ አግባብ የታሰሩትን ማስፈታት፣ ለበርካታ ጊዜያት ታስረው ለተፈቱት ደግሞ ካሳ የማሰጠት እና በሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ላይም ሊሰራ እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡
ለተነሱት ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽ የሰጡት የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ፤ ቦርዱ በርካታ ርቀቶችን ተጉዞ ብዙ ተግባራትን ማከናወኑን ገልጸዋል፡፡
ፓርቲዎችም ቦርዱ ያላያቸው ሂደቶች አሉ ብለው የሚያስቡ ከሆነም ወደ ሌሎች ዴሞክራሲያዊ ተቋማት በመሄድ መፍትሄ ማግኘት የሚችሉ መሆኑንም ተቁመዋል፡፡
በተያያዘም በውይይቱ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፋይናንስ አስተዳደር ስርዓትን ለማዘመን በተዘጋጀ መመሪያ ዙሪያም ውይይት ተካሂዷል፡፡
መመሪያውም ፓርቲዎች ከመንግስት የሚያገኙትንም ሆነ የሚሰባስቡትን ገንዘብ እንዲሁም ከተለያየ ምንጮች የሚያገኗቸውን ገቢዎች ለታለመው ዓለማ ብቻ እንዲያውሉት ያደርጋል ተብሏል፡፡
በተጨማሪም ተገቢ የሆነ የውስጥ ቁጥጥር ስርዓት እንዲኖር የሚያሥችል መሆኑንም በውይይቱ ላይ ተጠቁሟል፡፡