ቀጥታ፡

በመንግስት ተቋማት ሌብነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በስፋት እየተስተዋሉ በመሆኑ መንግስት ለመፍትሄው ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል

አርባ ምንጭ፣ ሚያዚያ 06/2014( ኢዜአ) በመንግስት ተቋማት ሌብነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በስፋት እየተስተዋሉ በመሆኑ መንግስት ለመፍትሄው ቅድሚያ ሰጥቶ እንዲሰራ  የአርባ ምንጭ ከተማ ሴቶች ጠየቁ ።

የሴቶች ሁለንተናዊ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ከተማ አስተዳደሩ አቅዶ እየሠራ መሆኑም ተመላክቷል።

"የፈተናዎች መብዛት ከብልፅግና ጉዟችን አያስቆመንም “በሚል መሪ ሃሳብ ከተማ አቀፍ የሴቶች የውይይት መድረክ ዛሬ በአርባ ምንጭ ከተማ ተካሂዷል።

በውይይቱም በመንግስት ተቋማት ሌብነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በስፋት እየተስተዋሉ በመሆኑ መንግስት ለመፍትሄው ቅድሚያ ሰጥቶ እንዲሰራ ጠይቀዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች በመንግስት መዋቅር ውስጥ ሆነው ከአሸባሪዎች ጋር በማበር የህዝቡን ሰላም የሚያውኩ አካላትንም ለይቶ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት አመልክተዋል።

ከተሳታፊዎች መካከል ወይዘሮ ትግላዊት ቡቼና "በከተማው በአንዳንድ ጥቅመኞች የተነሳ አሁንም ፍትሃዊ የሥራ ዕድልና ቅጥር ባለመኖሩ የሥራ አጡ ቁጥር እየጨመረ መጥቷል፤ መንግስት ትኩረት ይስጠው" ሲሉም ተናግረዋል።

"የኑሮ ውድነትን ለማቃለል በልማቱ ያለንን ተሳትፎ ማሳደግ ይገባል" ያሉት አስተያየት ሰጪዋ፣ ሰው ሰራሽ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር በህገወጥ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል።

ሀገራዊ ለወጡን ተከትሎ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ መንግስት በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ የገባውን ቃል በተግባር እንዲያረጋግጥም ጠይቀዋል።

ወይዘሮ ዓለሚቱ ገረሱ በሰጡት አስተያየት ሴቶችን በሁሉም መስክ ተጠቃሚ በማድረግ  የውሳኔ ሰጪነት ሚናቸውን ማሳደግ ይገባል።

ተስፋ ሰጪ ተግባራት እየተከናወኑ ቢሆንም "የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በአስተማማኝ ደረጃ ማድረስ ያስፈልጋል" ብለዋል።

የአርባ ምንጭ ከተማ ከንቲባ አቶ ማርቆስ ማቲዮስ በበኩላቸው “በመድረኩ ከሴቶች የተነሱ ጥያቄዎችን በሚቀጥሉት 90 ቀናት ዕቅድ እንዲሁም በመካከለኛ እና በረዥም ጊዜ ዕቅዶች ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ይሠራል” ብለዋል። 

ሴቶችን ያላሳተፈ የትኛውም ልማት ሊረጋገጥ እንደማይችል ተናግረዋል።

ሴቶች በተሳተፉበት ታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴው ግድብ ግንባታና እና የህልውና ዘመቻው አመርቂ ውጤት መገኘቱን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

ለሀገር ልማት እና ሰላም ታላቅ ገድል የፈጸሙ በርካታ ሴቶች መኖራቸውን ያስታወሱት ከንቲባው፣ የሴቶችን አቅም ለመጠቀም ምቹ መደላድል እየተፈጠረ መሆኑን ጠቁመዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢና የብልጽግና ፓርቲ የሴቶች ሊግ ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ  ህብረ ብሔራዊ አንድነትን አጠናክሮ በማስቀጠል በመንግስት ተቋማት የሚፈጸሙ ሌብነቶችን በጋራ መከላከልና ልማትን ማፋጠን እንደሚገባም አስገንዝበዋል።


ዴሞክራሲን በተጨባጭ ከማስፈን፣ የብሔርና የሀይማኖት ፅንፈኝነትን ከመከላከል እና የህዝቡን ሰላም በዘላቂነት ከማረጋገጥ አኳይ ክፍተቶች እንዳሉ ወይዘሮ ሸዊት ቢዚሁ ጊዜ ገልጸዋል።

በገበያው ለሸቀጦች የዋጋ መረጋጋት የንግድ ሥርዓቱ ሚዛናዊ እንዲሆን መንግስት የበኩሉን ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ሴቶችም በከተማ ግብርና በመሰማራት የምግብ ዋስትና ችግርን ለመቅረፍ የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በየአካባቢው አስተማማኝ ሰላም እንዲረጋገጥም ሴቶች ለሰላም ዘብ በመቆም የጀመሩትን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

መንግስት ለሚፈታቸው ችግሮች በቅርቡ በተደረገ የብልፅግና ፓርቲ አጠቃላይ ጉባኤ ላይ አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸው፣ በየደረጃው ያሉ አስፈጻሚ አካላት ለተግባራዊነቱ ክትትል እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

ከወይይቱ በኋላ ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ “ምግብን ከጓሮዬ፤ ጤናዬን ከምግቤ” በሚል መሪ ቃል ይፋዊ የከተማ ግብርና ሥራን ማስጀመራቸውን ኢዜአ ከስፍራው ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም