የአብሮነት፣ የመረዳዳትና የመዋደድ እሴቶቻችን የሁል ጊዜ መገለጫዎቻችን ሊሆኑ ይገባል-የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች

መቱ ሚያዝያ 6/2014 (ኢዜአ) የአብሮነት፣ የመረዳዳትና የመዋደድ እሴቶቻችን በሀይማኖታዊ ክብረ በዓላት ወቅት ብቻ ሳይወሰኑ የሁልጊዜ መገለጫዎቻችን ሊሆኑ ይገባል ሲሉ በኢሉ አባቦር ዞን የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች አስገነዘቡ። 

"ካለን ነገር ለሌላቸው የማካፈልና ፍቅራችንን ያለልዩነት በተግባር ማሳየት የቆዩ እሴቶቻችን በመሆናቸው ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው " ሲሉም  የኃይማኖት አባቶቹና የሀገር ሽማግሌዎች ለኢዜአ አስታውቀዋል ።

በኢሉ አባቦር ዞን ሁሩሙ ወረዳ የተለያዩ ኃይማኖቶች ተከታዮች የታደሙበት የአደባባይ አፍጥር ስነ ስርአት ትላንት ምሽት ተካሄዷል።

በስነ ስርአቱ ላይ የታደሙ "የሀገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት አባቶች "የኅብረተሰቡ የቆየ የአብሮነት፣ መረዳዳትና የመዋደድ እሴቶች የሁልጊዜ መገለጫዎቻችን እንዲሆኑ ጠንክረን እንሰራለን" ብለዋል።

በወረዳው የሁሩሙ ቢላል መስጂድ ኢማም ሼህ ጀማል ሁሴን "ባለንበት የፆም ወቅት ካለን ነገር ለሌላቸው በማካፈልና በመረዳዳት አብሮነታችንን ማሳየት አለብን" ብለዋል።

ሼህ ጀማል አክለውም "የአብሮነት፣ መረዳዳትና መዋደድ እሴቶቻችን በየኃይማኖቶቻችን በሚኖሩን ክብረ በዓላት ወቅት ብቻ ሳይሆን የሁልጊዜ መገለጫዎቻችን ሆነው እንዲቀጥሉ ልንሰራባቸው ይገባናል" ሲሉ አክለዋል ።

"የኃይማኖት፣ የብሔር፣ የቋንቋና ሌሎች ልዩነቶቻችንን በማክበር በጋራ መቆማችን ለማኅበራዊውም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻችን እንደመፍቻ ቁልፍ ያገለግለናል" ያሉት ደግሞ  የሀገር ሽማግሌ ኢብራሂም ከድር ናቸው።

"ለቀጣዩ ትውልድ የመረዳዳት፣ የመዋደድ የአብሮነት ዕሴቶችን የማስተማር፣ የማሳየትና የማስተላለፍ ኃላፊነቱ የኛ የታላላቆቹ እንደመሆኑ ለልጆቻችን አርዓያ መሆን አለብን" ብለዋል ።

የሁሩሙ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አሰፋ ረጋሳ በስነ ስርአቱ ላይ እንዳሉት በሀገራችንም ሆነ አንደየ አከባቢያችን ለዘመናት የኖሩ የመቻቻል፣ የመረዳዳትና የአብሮነት እሴቶቻችን ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል።

"ይህ ሲሆን በሀገራችን ሁለንተናዊ ልማት ውስጥ በጋራ በመሳተፍ ሀገር እናሳድጋለን " ብለዋል ።

"በሁሉም መስክ የሚኖረን አንድነት ለሰላምና ለዕድገታችን ወሳኝ በመሆኑ እንዲጎለብት መስራት አለብን" ሲሉም  አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም