በሳኡዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ካሉ ዜጎች መካከል እስካሁን ከ7 ሺህ በላይ ወደ አገር ቤት መመለስ ተችሏል

ሚያዝያ 06 ቀን 2014 (ኢዜአ) በሳኡዲ አረቢያ እስር ቤቶች እና ማቆያ ማዕከላት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ካሉ ዜጎች መካከል እስካሁን ከ7 ሺህ በላይ ወደ ኢትዮጵያ መመለስ መቻሉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤ በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ በሳምንቱ የተከናወኑ አንኳር ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸው በሳምንቱ ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ማብራሪያ መሰጠቱን ጠቅሰዋል።

በዚህ መሰረት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አማካኝነት ለየሀገራቱ አምባሳደሮችና አለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ገለፃ የተደረገላቸው ስለመሆኑ አምባሳደር ዲና ተናግረዋል።

በተለይ ለትግራይ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት እየደረሰ ሰለመሆኑ እና በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ ላይ እየተደረጉ ያሉ ትችቶች ትክክል አለመሆናቸው ማብራሪያ እንደሰጡበት አምባሳደር ዲና ገልጸዋል።

በዚህም የሰብዓዊ መብት ድጋፍ አቅርቦት ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ ሳይቀመጥለት እየተደረገ መሆኑን እና ይሄ ተጠናክሮ እንዲሄድ ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ እንዲያደርግ መጠየቃቸውን ተናግረዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በአምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂውማን ራይትስ ዎች የወጣው ሪፖርት ከሰብዓዊነት ይልቅ ፖለቲካዊ ይዘቱ እንደሚያመዝን የገለፁት አምባሳደር ዲና መንግስት ጉዳዩን በቅርበት ለመመርመር ፍላጎት እንዳለው ማንሳታቸውንም ጠቁመዋል።

"ሪፖርቱ ለአንድ ወገን ያደላ እና ከሰብዓዊ ጉዳይ ውጪ የሆኑ አጀንዳዎች የተነሱበት" ነው ሲሉ ሪፖርቱ ላይ ወቀሳና ትችታቸውን አንፀባርቀዋል።

በሌላ በኩል ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙ ዳያስፖራ ተወካዮች ጋር ውይይት ማድረጋቸው አውስተዋል።

በውይይቱ በተለይም ኤች.አር 6600 እና ኤስ 3199 ረቂቅ ሕጎችን በመቃወም ዳያስፖራው እያደረገው ያለውን ጥረት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማድነቃቸው አንስተዋል።

ጥረቱ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አቶ ማሳሰባቸውን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

መንግስት ለሰላም ፍላጎት ያለው ቢሆንም በሀገር ሉዓላዊነት ላይ ግን ድርድር እንደሌለው ለዲያስፖራው ማሕበረሰብ ተወካዮች በውይይቱ ላይ ገለፃ መደረጉንም ቃል አቀባዩ ተጠቅሰዋል።

በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ፤ በሳኡዲ አረቢያ እስር ቤቶች እና ማቆያ ማዕከላት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ካሉ ዜጎች መካከል እስካሁን ከ7 ሺህ በላይ ወደ አገራቸው መመለሳቸውን ተናግረዋል።

በሳምንት ሶስት ቀናት፤ በቀን ሶስት ጊዜ ወደ አዲሰ አበባ በሚደረጉ በረራዎች ዜጎችን የመመለስ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም