የአምነስቲ እና የሂውማን ራይትዎች ሪፖርት ግልጽ ወገንተኛነት የተንጸባረቀበት ነው---ረዳት ፕሮፌሰር ቻላቸው ታረቀኝ - ኢዜአ አማርኛ
የአምነስቲ እና የሂውማን ራይትዎች ሪፖርት ግልጽ ወገንተኛነት የተንጸባረቀበት ነው---ረዳት ፕሮፌሰር ቻላቸው ታረቀኝ
ባህር ዳር (ኢዜአ) ሚያዚያ 6/2014 " የአምነስቲ ኢንተርናሽናልና የሂውማን ራይትዎች ሪፖርት ሳይንሳዊ ጥናት ላይ ያልተመሰረተና ግልፅ ወገንተኛነት የተንፀባረቀበት ነው" ሲሉ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህርና ተመራማሪ አስታወቁ።
በዩኒቨርሲቲው የዓለም አቀፍ ግንኙነትና የፖለቲካል ሳይንስ መምህርና ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር ቻላቸው ታረቀኝ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ድርጅቶቹ ሪፖርቱን ያወጡት የአሸባሪው ህወሓት ሰዎች በሰጧቸው የተሳሳተ መረጃ ላይ ተመስርተው ነው።
"አሸባሪው ህወሓት በወልቃይት፣ ጠገዴና ሁመራ ከፍተኛ የዘር ፍጅት መፈጸሙ ቢታወቅም በአሁኑ ወቅት በተጨባጭ ማስረጃ እየተረጋገጠ መጥቷል" ብለዋል።
ይሁን እንጂ ድርጅቶቹ ያወጡት ሪፖርት ከመረጃ ምንጭ አወሳሰድ ጀምሮ አንድ ጥናት ሊያሟላ የሚችለውን ዝቅተኛ መለኪያ እንኳ ማሟላት የማይችል እንደሆነ ተናግረዋል።
"ሪፖርቱ በተሳሳተ መረጃ ላይ ተመስርቶ የወጣ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም" ሲሉም ረዳት ፕሮፌሰሩ አመልክተዋል።
ረዳት ፕሮፌሰሩ አክለው "አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን በበላይነት ሲመራ በነበረበት ዘመን ለድርጅቶቹና በሥራቸው ለነበሩ አመራሮችና ሠራተኞች ከፍተኛ ዶላር ሲከፍሏቸው የነበሩ በመሆኑ ውለታቸውን ለመክፈል በማለም ያደረጉት ነው" ብለዋል ።
አሸባሪው ህወሓት በስልጣን ዘመኑ በአምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሂውማን ራይትዎች እንዲሁም በሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ የራሱን ሰዎች በመሰግሰግና የውጭ ጥቅመኞችን በገንዘብ በመግዛት አሁን በኢትዮጵያ ላይ ችግር እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።
መሬት ላይ ያለው እውነታ ድርጅቶቹ በየጊዜው የሚያወጡት ሪፖርት ለአሸባሪው ህወሓት የወገነና የተሳሳተ መሆኑን ስለሚያሳይ ድርጅቶቹን ተአማኒነት እያሳጣ መሆኑን ተናግረዋል።
"ድርጅቶቹ ይህን የሚያደርጉት የፖለቲካ ፍላጎታቸውንና ጥቅማቸውን ለማስፈጸም ነው" ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ "የተሳሳተ መረጃ በመፈብረክ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንደሚለቁ ከሪፖርታቸው እየተረዳን መጥተናል" ሲሉም አክለዋል።
መሬት ላይ ያለው እውነት ከሪፖርቱ በተቃራኒው መሆኑን የገለጹት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ "የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ባካሄደው ጥናት አሸባሪው ህወሓት በወልቃይትና በአካባቢው የዘር ጭፍጨፋ መፈጸሙን አረጋግጧል" ብለዋል።
በታሪካዊ ምርምር ተጨባጭ ማስረጃ ከሚባሉት የአጽም ግኝቶች መሆናቸውን ጠቁመው፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተጨባጭ የጥናት ግኝት አሸባሪውን ህወሓት በዓለም አቀፍ ደረጃ በዘር ፍጅት የሚያስጠይቅ መሆኑን ተናግረዋል።
ይሁንና ድርጅቶቹ ከራሳቸው ጥቅም በመነሳት በትግራይ ዜጎች ላይ ጭፍጨፋ ተፈጽሟል ብለው ሪፖርት ማውጣታቸው በወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ሁመራና አካባቢው ማህበረሰብ ላይ በህወሓት የተፈጸመውን የፍጅት ወንጀል በመሸፋፈን ህወሓትን ከተጠያቂነት ለማዳን ያለመ መሆኑን አስረድተዋል።
"የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ የተባሉት ድርጅቶቹ ከምዕራባውያን መንግስታት ጋር የተሳሰሩ በመሆናቸው የምዕራባውያን ፖለቲካ ማስፈጸሚያ መንገዶች መሆናቸውን ሁሉም ሊያውቀው ይገባል" ሲሉ ረዳት ፕሮፌሰሩ አክለዋል።
የፌደራልም ሆነ የክልል መንግስታት ሪፖርቱን በአግባቡ በመመርመር ተገቢውን ምላሽ ፈጥኖ በመስጠት ውድቅ ማድረግ እንዳለባቸው አመልክተዋል።
"መገናኛ ብዙሀንም ለአፍሪካ አገራትና በየትኛውም ዓለም ለሚገኙ የኢትዮጵያ ወዳጅ አገራት በተከታታይ ዘገባ አውነታውን በማሳየት የድርጅቶቹን የፖለቲካ ወገንተኝነትና ሴራቸውን ማጋለጥ ይገባል" ሲሉ አስገንዝበዋል።
ረዳት ፕሮፌሰሩ እንዳሉት ድርጅቶቹ የአፍሪካ የሰላም አስከባሪ እንዲገባ ያመላከቱት በኢትዮጵያ ሉአላዊነት ላይ ጣልቃ በመግባት ለአሸባሪ ቡድኑ መውጫና መግቢያ ቀዳዳ ለመፍጠር በማለም ነው።
ከውጭም ሆነ ከውስጥ የሚቃጣ አደጋን በመቋቋም ኢትዮጵያን ከመፍረስ አደጋ ለመታደግ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነቱን ማጠናከር እንዳለበት ረዳት ፕሮፌሰር ቻላቸው አስገንዝበዋል።