የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተክርስቲያን የልማት ኮሚሽን ለተፈናቃዮች በ43 ሚሊዮን ብር የምግብ እህል ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተክርስቲያን የልማት ኮሚሽን ለተፈናቃዮች በ43 ሚሊዮን ብር የምግብ እህል ድጋፍ አደረገ
ደሴ፣ ሚያዝያ 05 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተክርስቲያን የልማት ኮሚሽን ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በደቡብ ወሎና ሰሜን ወሎ ዞኖች ለተጠለሉ ወገኖች 43 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የምግብ እህል ድጋፍ አደረገ።
የልማት ኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶክተር ተፈራ ተሎሬ የድጋፍ ስርጭቱን ዛሬ በኩታ በር ከተማ ተገኝተው ባስጀመሩበት ወቅት በተለያዩ የልማት ሥራዎች ህዝቡን እያገዘ የሚገኘው ኮሚሽኑ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በዞኖቹ ለተጠለሉ ወገኖች ከ7 ሺህ 600 ኩንታል በላይ የምግብ እህልና 23 ሺህ ሊትር የምግብ ዘይት ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።
የተለያዩ የረድኤት ድርጅቶችን በማስተባበር የተደረገው ድጋፍ ከ23 ሺህ ለሚበልጡ ተፈናቃይ ወገኖች እንደሚሆን አመልክተዋል።
ለተጠቃሚዎቹ በነፍስ ወከፍ 15 ኪሎ ግራም የስንዴ ዱቄት፣ 2 ኪሎ ግራም ባቄላ፣ 1 ነጥብ 5 ሊትር ዘይትና ሌሎችም አልሚ ምግቦች እንደሚደርስ ጠቁመዋል።
የልማት ኮሚሽኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ዜጎች በዘላቂነት እንዲቋቋሙ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ዶክተር ተፈራ አስታውቀዋል።
በአማራ ክልል ፋይናንስ ቢሮ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ክትትልና ግምገማ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ መሀሪ ምንተስኖት በበኩላቸው የክልሉ መንግስት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን በዘላቂነት ለማቋቋምም እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
መንግስት ለተፈናቃይ ወገኖች የእለት ምግብ ተደራሽ ለማድረግና መልሶ ለማቋቋም የሚያደርገውን ጥረት ሌሎች አካላት እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተክርስቲያን የልማት ኮሚሽን ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በተለያየ ጊዜ በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ ችግሮች ለችግር ለተጋለጡ 61 ሺህ ዜጎች ከ161 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የምግብ እህል ድጋፍ ማድረጉን ከልማት ኮሚሽኑ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ