ወደ ውጭ ከሚላኩ ምርቶች የሚገኘው ገቢ ለማሳደግ ለጥራት ትኩረት መስጠት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ወደ ውጭ ከሚላኩ ምርቶች የሚገኘው ገቢ ለማሳደግ ለጥራት ትኩረት መስጠት ይገባል
ድሬዳዋ፣ ሚያዝያ 5/2014(ኢዜአ) ወደ ውጭ ከሚላኩ የተለያዩ ምርቶች የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ለጥራት ትኩረት መስጠት እንደሚገባ የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ቦንሣ ባይሣ አሳሰቡ።
ኢንስቲትዩቱ የጥራት ደረጃዎች ምንነትና አስፈላጊነት ላይ በምሥራቅ ኢትዮጵያ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት እንዲሁም በማር ምርት ላይ ለተሰማሩ አምራቾች በድሬዳዋ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አካሄዷል።
ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ በኢንዱስትሪውም ሆነ በግብርና ዘርፍ ጥራትና ደረጃን ጠብቆ ማምረት የህልውና ጉዳይ ነው፡፡
እስከ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ያሉት ተዋናዮች በዓለም አቀፍ ንግድና ገበያ ላይ መቆየት የሚቻለው ተቀናጅቶ ጥራት የሚያስጠብቁ ምርቶችን በማምረት ነው ብለዋል፡፡
ለዚህም ወደ ውጭ ከሚላኩ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ለማሳደግና የማህበረሰቡን ጤና ለመጠበቅ ለጥራት ትኩረት መስጠት እንደሚገባ አሳስበዋል።
ኢንስቲትዩቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚያደርግ አቶ ቦንሣ ገልጸዋል፡፡
በኢንስቲትዩቱ የደረጃዎች ዝግጅት ዳይሬክተር አቶ ይልማ መንግሥቱ በበኩላቸው፤ ተቋማቸው እስካሁን ከ12 ሺህ በላይ ደረጃዎች ቢያወጣም፤ በሚፈለገው ያህል ወደ ትግበራ አለመግባታቸውን ተናግረዋል፡፡
ተቋማት ኢንስቲትዩቱ ያወጣቸውን ደረጃዎች ሥራ ላይ በማዋል ለሀገር ሁለንተናዊ ዕድገትና ተጠቃሚነት ሚናቸውን እንዲጫወቱ አመልክተዋል፡፡
የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ ባለሙያ ወጣት ነጋሽ አበበ በሰጠው አስተያየት ፤ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ በየደረጃው ለሚገኘውና ለሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ቢሰጥ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ተናግሯል፡፡
በመድረኩ ከሐረሪ፣ከኦሮሚያና ከሶማሌ ክልሎች እንዲሁም ከድሬዳዋ አስተዳደር የተውጣጡ ማር አምራቾች፣ በአልባሳትና ጨርቃ ጨርቅ ዘርፎች የተሰማሩ አካላት እንዲሁም የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡