ቀጥታ፡

የዴሞክራሲ ተቋማት በህዝቦች መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተን አንድነት ለማስረፅ መስራት ይጠበቅባቸዋል - የፌዴሬሽን ምክር ቤት

አዳማ ፤ ሚያዝያ 05/2014(ኢዜአ) የዴሞክራሲ ተቋማት በህዝቦች እኩልነትና መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተን አንድነት ለማስረፅ በሙሉ አቅማቸው መስራት እንደሚጠበቅባቸው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አሳሰበ።

ምክር ቤቱ "በዴሞክራሲያዊ ባህል ግንባታ የዴሞክራሲ ተቋማት ያላቸው ሚና" በሚል መርህ ሐሳብ  ከባላድርሻ አካላት ጋር ዛሬ በአዳማ ከተማ መክሯል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል  አፈ  ጉባኤ ወይዘሮ ዘሓራ ሁመድ በወቅቱ እንዳሉት፤  የዴሞክራሲያዊ ባህል ግንባታ እውን የሚሆነው የብዙሃኑን ፍላጎትና ተሳትፎ ባረጋገጠ መልኩ መተግበር ሲቻል ነው።

በተለይም በህዝቦች እኩልነትና በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተን አንድነት ለማስረፅ የዴሞክራሲ ተቋማቱ በዴሞክራሲያዊ ባህል ግንባታ ላይ በሙሉ አቅማቸው እንዲሰሩ ማስቻል ይገባል ነው ያሉት።

የምክክር መድረኩ የተዘጋጀውም  ተቋማቱ የዴሞክራሲያዊ ባህል ግንባታ ተግባራትን በተናበበ መልኩ ማሳካት እንዲችሉ ለማመቻቸት መሆኑን ገልጸዋል።

ብዙሃነትን መቀበልና ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ማጠናከር ከተቋማቱ የሚጠበቅ አብይ ጉዳይ መሆኑን የተናገሩት  ወይዘሮ ዘሃራ፤ በተለይም ተቋማቱ ጠንካራ  አደረጃጀቶች እንዲኖራቸው፣  ፍትሃዊና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ቁመና እንዲይዙ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ሀገራችን ዴሞክራሲያዊ ባህልና ስርዓት ያልዳበረባት በመሆኑዋ ከእነዚህ የዴሞኪራሲ ተቋማት ዘርፈ ብዙ ስራዎች ይጠበቃሉ ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ዋና እንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ሃይሌ ናቸው።

ተቋማቱ በተለይም ነጻና ገለልተኛ ሆነው በአስፈጻሚው ላይ ተጠያቂነትና በህዝቦች መካከል እኩልነት እንዲሰፍን፣ መቃቃር ሳይሆን መቻቻል፣ በአብሮ ማደግና መልማት እንዲቻል በጋራ የሚመሩበት እቅድ አውጥተው በአዋጁ በተሰጣቸው ልክ መስራት ግዴታቸው መሆኑን አስረድተዋል።

የህገ መንግስትና ፌዴራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል ዳይሬክተር ዶክተር ሃይለየሱስ ታዬ፤  ተቋማቱ ራሳቸውን ችለው መውጣትና ዘላቂ ተቋማት ሆነው መቀጠል አለባቸው እንጂ ከፓርቲና አስተዳደሩ ጋር የሚቀየሩ መሆን የለባቸውም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም