ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተመረቁ ወጣቶችን በማደራጀት የመስሪያና መሸጫ ሼዶች ተሰጠ

ሀዋሳ፤ ሚያዚያ 5/2014 (ኢዜአ) የሃዋሳ ከተማ አስተዳደር ከተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመርቀው ስራ ያላገኙ ወጣቶችን በማደራጀት የመስሪያና መሸጫ ሼዶችን መስጠት ጀመረ፡፡

በርክክቡሥነሥርዓትላይየከተማዋ አስተዳደር ከንቲባረዳት ፕሮፌሰር ጸጋዬ ቱኬ፤ ወጣቶችን በሁሉም ዘርፍ ተጠቃሚ በማድረግ በከተማዋ እድገትና ብልጽግና የድርሻቸውን እንዲወጡ ይሰራል ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ ከ25 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃንን የስራ እድል ተጠቃሚ ለማድረግ በልዩ ሁኔታ ወደ ስራ መገባቱንም  ገልጸዋል።

መንግስት ለስራ እድል ፈጠራ በሰጠው ትኩረትበከተማው ስራ ያላገኙ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተመረቁ 1ሺህ 683 ወጣቶች  መለየታቸውን አመልክተው፤ከተለዩትም 1ሺህ 10 የሚሆኑት በቂ ስልጠና ወስደውና ተደራጅተው ለስራ ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ለእነዚህም  የማምረቻናመሸጫ ሼድ  የማስተላለፍ  ስራ መጀመሩን ያስታወቁት ከንቲባው፤ የስራ እድል ተጠቃሚ የሆኑ ወጣቶች ጠንክረው በመስራት ከራሳቸው አልፎ ለሀገር መጥቀም እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የመስሪያ ማምረቻና መሸጫ ሼድ የተረከቡት በንግድና አገልግሎት ዘርፍ በ82 ማህበራት የተደራጁ ወጣቶች መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የሃዋሳ ከተማ ስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት መምሪያ ሃላፊ አቶ ታረቀኝ ዳሪሞ ናቸው።

ባለፉት ሁለት ወራት በልዩ ሁኔታ የከፍተኛ ትምህርት ምሩቃንን ከመንግስት መስሪያ ቤት ቅጥር ጠባቂነት አመለካከት ለመቀየር ጥረት መደረጉን ገልጸዋል።

ወጣቶቹ የክህሎትና የተለያዩ ለስራቸው የሚጠቅሙ ስልጠናዎች መውሰዳቸውን የገለጹት ሃላፊው፤የመስሪያሼዶችንከማስተላለፍ በተጨማሪከ30 ሚሊየን ብር በላይ ብድር መዘጋጀቱንም አስታውቀዋል።

ወጣቶቹ ውጤታማ እንዲሆኑ በብድር አቅርቦት፣ በስልጠናና በገበያ ትስስር በቂ ድጋፍ በማድረግ ወደ ኢንዱስትሪ እንዲሸጋገሩ ድጋፍ እንደሚደረግ አቶ ታረቀኝ ጠቁመዋል፡፡

የሲዳማክልል ርዕሰ መስተዳድር ልዩ አማካሪ አቶ ተሰማ ዲማ በበኩላቸው፤ ወጣቱን ወደስራ ማሰማራት የሚፈለገውን ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል  አቅም ስላለው ነው  ብለዋል።

እንደ ክልል በበጀት ዓመቱ ከ92ሺ በላይ ወጣቶችን ወደ ስራ ለማሰማራት የተያዘውን እቅድ ለማሳካት የሃዋሳ ከተማ አስተዳደር ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

የስራ እድሉ ተጠቃሚ ከሆኑ ወጣቶችመካከል ከሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ በማርኬቲንግ ማኔጅመንት በ2010 ዓ.ም የተመረቀው ይስሃቅ ሰቄቻ በተረከቡት የመሸጫ ሼድ በንግድ ዘርፍ ለመሰማራት የክህሎት ስልጠና መውሰዳቸውን ገልጾ የተሻለ ስራ በማከናወን ተወዳዳሪ ለመሆን ራሱን ማዘጋጀቱን ተናግሯል።

በርክክቡ ሥነሥርዓት ላይ የክልሉናየከተማአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች መገኘታቸውን ኢዜአ ከሀዋሳ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም