ቀጥታ፡

በከፍተኛ እዳ ውስጥ የነበሩ የልማት ድርጅቶችን ሕልውና ለመታደግ የተሰሩት ሥራዎች ውጤታማ ሆነዋል

ሚያዚያ 5/2014 (ኢዜአ) በከፍተኛ እዳ ውስጥ የነበሩ የልማት ድርጅቶችን ሕልውና ለመታደግና ማክሮ ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት የተወሰደው እርምጃ ውጤታማ መሆኑን የዕዳና የኃብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን ገለጸ ።

በአግባቡ ባልተጠና የኢኮኖሚ አማራጮች ወደ ሥራ የገቡ የልማት ድርጅቶች አገሪቱን ለከፋ ኪሳራና ለማክሮ ኢኮኖሚው አለመረጋጋት ሥጋት ሆነው ቆይተዋል።

ባለፈው ዓመት መንግሥት የልማት ድርጅቶች ያለባቸውን ከፍተኛ የዕዳ ጫና የሚያስተዳድር "የዕዳና የኃብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን'' በአዋጅ አቋቁሟል።

ተቋሙም ለኢኮኖሚው ሥጋት ሆነው የቆዩና ከፍተኛ የዕዳ ጫና ውስጥ ወድቀዋል ተብለው የተለዩ ስድስት ተቋማት እዳ ወስዶ ወደ ሥራ እንዲገቡ አድርጓል።

በመንግሥት የተለዩት ስድስቱ የመንግሥት ልማት ድርጅቶችም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን፣ ኢትዮ-ኢንጂነሪንግ ግሩፕ (የቀድሞው ሜቴክ)፣ ኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽንና የስኳር ኮርፖሬሽን ናቸው።

የዕዳና የኃብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሙሉዓለም ጌታሁን እንደገለጹት፤ የልማት ድርጅቶቹ ሲቋቋሙ የኢኮኖሚ አዋጭነታቸው በአግባቡ ተጠንተው ባለመሆኑ መንግሥትን ለከፍተኛ ኪሳራ ዳርገውታል።

እነዚህ ድርጅቶች ከአገር ውስጥ አበዳሪዎች በዋናነት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ከውጭ አበዳሪዎች ተበድረው ያልመለሱት በርካታ ገንዘቦች አሉ።

ኮርፖሬሽኑም ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች ከሚያተርፉት ትርፍ ከሚገኘው የትርፍ ድርሻ (ዲቪደንድ) እና ከአበዳሪ ተቋማት ጋር በመነጋገር እዳውን ለመክፈል ይሰራል።

ኮርፖሬሽኑ በአዋጅ ሲቋቋም ለተቋሙ መንግሥት የፈቀደለት 570 ቢሊዮን ብር ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 142 ቢሊዮን ብሩ በጥሬ ገንዘብና በአይነት ተከፍሎታል።

በዚህም በቅርቡም የኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮ-ኢንጂነሪንግ ግሩፕና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ  አገልግሎት እዳዎችን መዝጋቱን ጠቁመዋል።

ለዚህም ለንግድ ባንክ 34 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር መከፈሉን ገልጸዋል።

ማክሮ ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት የተወሰደው ተቋማዊ አደረጃጀት የልማት ድርጅቶችን ሕልውና እየታደገ እንደሆነ አቶ ሙሉዓለም ጠቁመዋል።

የተቋማቱን እዳ ለመክፈል የተዘረጋው አሰራር  በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ እንዲገቡ ከማድረግ ባለፈ  ለማክሮ ኢኮኖሚ ሥጋት የመሆን ዕድላቸውን ቀንሷል።

የቀሩት ተቋማት ፋይናንስ የማፈላለግ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ እንዲገቡ ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።

ኮርፖሬሽኑ የተረከበውን ብድር ከኢንዱስትሪ ልማት ፈንድና ከሌሎች የፋይናንስ ምንጮች በማፈላለግ እንደሚከፍል በአዋጁ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም