ቀጥታ፡

የምስራቅ አፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና በኢትዮጵያ አስተናጋጅነትይካሄዳል

ሚያዚያ 5/2014 (ኢዜአ) የምስራቅ አፍሪካ የአዋቂዎች የጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት እንደሚካሄድ ፌዴሬሽኑ ገለጸ።

ኢትዮጵያ ይህንን የምስራቅ አፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና የምታዘጋጀው ከ28 ዓመት በኋላ ነው።  

ውድድሩ ከሚያዚያ 27 እስከ 30/2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ስፖርት አካዳሚ ይካሄዳል ተብሏል።

በውድድሩ ከ14 አባል አገራት መካከል እስካሁን 11 አገራት ለመሳተፍ ማረጋገጫ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ተስፋዬ ብዛኔ፤ ውድድር በተሳካ መልኩ ለማካሄድ  ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።

ውድድሩ በኢትዮጵያ አዘጋጅነት መካሄዱ በቀጣይ የአፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ውድድሮች ለማዘጋጀት ልምድ ለማግኘት ጠቃሚ ነው።

አሁን ላይ አገሪቱ የውጭ ምንዛሬ እንድታገኝ፣ ቱሪዝምና ለሆቴሎች ጥሩ አጋጣሚ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ኢትዮጵያ ለዚህ ውድድር በተለያዩ ውድድሮች የተሻለ አቅም ያላቸው ስፖርተኞች መመረጣቸውን ገልጸዋል።

በውድድሩም 10 ወንድና 10 ሴት አትሌቶችን እንደምታሳትፍ ነው ፕሬዝዳንቱ የተናገሩት።

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ፌዴሬሽኖች አባል ከሆነችባቸውና ረጅም እድሜ ካላቸው መካከል አንደኛው የጠረጴዛ ቴኒስ ሲሆን የዓለም አቀፉ ጠረጴዛ ቴኒስ አባል የሆነችው 1964 ዓ.ም መሆኑ ከፌዴሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም