የሀገር ሽማግሌዎች ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት ባህላዊ የግጭት አፈታት እሴቶች ይጠቀማሉ

271

ሆሳዕና ሚያዚያ 4/2014 (ኢዜአ) ለሀገራዊ የምክክር መድረክ እንዲሳካ ባህላዊ የግጭት አፈታት እሴቶችን በመጠቀም ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ የስልጤ ዞን የሀገር ሽማግሌዎች ገለጹ፡፡ 

 ኢትዮጵያ ቀደምት ታሪክ ያላትና ባህላዊ እሴቶቿን በመጠቀም ራሷን በራሷ ስታስተዳድር የኖረች ሀገር መሆኗን በስልጤ ዞን የዳሎቻ ከተማ ሀገር ሽማግሌ አቶ ሁሴን ሱንከሞ ገልጸዋል፡፡

የተለያዩ ምክንያቶች ለሚያጋጥሙ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ በማምጣት ረገድ የባህላዊ እሴቶች ሚና ከፍተኛ  መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በአካባቢቸው የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በባህላዊ መንገድ የመፍታት ልምድ እንዳላቸው ገልጸው፣ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ባህላዊ የግጭት አፈታት እሴቶችን መጠቀም ያስፈልጋል ይላሉ፡፡

ሀገሪቱ ሊካሄድ ለታሰበው ሀገራዊ የምክክር መድረክ ስኬት ባህላዊ እሴቶችን በመጠቀም አብሮነት እንዲጠናከርና የህዝብ ለህዝብ ትስስር በማጠናከር ኃላፊነታቸው እንደሚወጡ ገልጸዋል፡፡

በምስራቅ ስልጢ ወረዳ የላሎ ቀርሶ ቀበሌ የባህል ሽማግሌ ሐጂ ሸምሱ ከድር እንዳሉት ቀደምት አባቶቻችን ፍትህ እንዳይጓደል ባህላዊ የዳኝነት ስርዓትን በመጠቀም መፍትሄ ያመጡ ነበር።

የአንዱን ችግር ሌላኛው በመጋራት፣ በደቦ ተደራጅተው በመስራት የመረዳዳትና የመተባበር፣ አብሮነትን የማጠናከር ባህል ዛሬም ድረስ በገጠሩ ኅብረተሰብ እየተተገበረ ነው ብለዋል፡፡

ባህላዊ እሴቶችን በመጠቀም ለምክክር መድረኩ ስኬታማነት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱም ሐጂ ሸምሱ ተናግረዋል፡፡

"እንደ ሀገር ሊካሄድ በታሰበው የምክክር መድረክ አብሮነትን ለማጠናከር በሚረዱ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ይገባል’’ ያሉት ሌላኛው የሀገር ሽማግሌ አቶ መኬጂ ሙሳ ናቸው፡፡

አንደ አካባቢው ባህል ያላቸውን ልምድ ተጠቅመው ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት የድርሻቸውን እንደሚያበረክቱም አረጋግጠዋል።

የምክክር መድረኩ በርካታ  ሀገራዊ ችግሮችን ይፈታል የሚል አምነት እንዳላቸው የሀገር ሽማግሌው አቶ መኬጂ ሙሳ ገልጸዋል፡፡

ቀደምት አባቶች ነፃነቷ የተጠበቀ ሀገር ያቆዩልን በሀገር ጉዳይ ላይ በአንድ አመለካከት መጓዝ በመቻላቸው መሆኑን ጠቅሰው፣ ለሀገራዊ ለምክክሩ ስኬት በጋራ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም