በኮንትሮባንድ የገባ ከ10 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ልባሽ ጨርቅ በቁጥጥር ስር ዋለ

462

ደሴ፤ ሚያዚያ 5/2014(ኢዜአ) በኮንትሮባንድ የገባ ከ10 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ልባሽ ጨርቅ ሐሰተኛ ሰነድ በመጠቀም ለማሳለፍ ሲሞከር በቁጥጥር ስር መዋሉን በኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን የኮምቦልቻ ቅርንጫፍ አስታወቀ፡፡

በሰሌዳ ቁጥራቸው ኮድ 3-00812 ኢት እና በኮድ 3-99929 ኢት ከባድ ተሸከርካሪዎች ልባሽ ጨርቁን በኮንቴነሮች ጭነው እያጓጓዙ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሀገረ ማሪያም ከተማ እንደደረሱ መቆጣጠር እንደተቻለ የቅርንጫፉ  የደንበኞች ትምህርት ቡድን አስተባባሪ አቶ አሳምነው አዳነ ለኢዜአ ተናግረዋል።

 ወደ አዲስ አበባ ለማሳለፍ የነበረው ልባሽ ጨርቁ  በጉምሩክ ሰራተኞችና በአማራ ክልል የጸጥታ ሃይሎች ባደረጉት የተቀናጀ ጥረት መቆጣጠር መቻሉን ገልጸዋል።

ሐሰተኛ ሰንድ በመጠቀም ለማሳለፍ የሞከሩ ሁለቱም አሽከርካሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በህግ እየታየ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

የሃገረ ማርያም አካባቢ ህብረተሰብ ይህንን ህገ ወጥ ድርጊቱ ለመቆጣጠር ጥቆማ በመስጠት ላደረገው ትብብር ምስጋና አቅርበዋል።

ኮንትሮባንድ ኢኮኖሚውን በማዛባት ሃገርና ህዝብን የሚጎዳ በመሆኑ  ድርጊቱን ለማስቆም ህብረተሰቡ እየሰጠ ያለውን ድጋፍ  እንደቀጥልም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም